አዳማ ጥቅምት 9/2019 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ከተለያዩ ቆጠራና ጥናቶች የሚያመነጫቸውን የስታቲስቲክ መረጃ ሪፖርት ውጤቶችን ለተጠቃሚዎች ለአጠቃቀም ቀላል፤ ምቹና ሳቢ በሆነ መልኩ ለማዘጋጃት በሚያግዝ ፓወር ቢአይ (Power BI) ሶፍት ዌር ላይ ከተቋሙ ዋና መስሪያ ቤት የተለያዩ የስራ ክፍሎች ለተወጣጡ መሪ ስራ አስፈጻሚዎች፣ የዴክስ ኃላፊዎችና ከፍተኛ ባለሙያዎች በአዳማ ከተማ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።
በመድረኩ ተገኝተው ስልጠናውን ያስጀመሩት የተቋሙ የስታቲስቲክስ ሲስተም ልማትና የሜቶዶሎጅ ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ጃሚላ ሙሀመድ ኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ከተለያዩ ቆጠራና ጥናቶች የሚያመነጫቸውን የስታቲስቲክ መረጃ ሪፖርት ውጤት ዝግጅት ተጠቃሚዎች በቀላሉ የሚረዱት ምቹና ሳቢ ለማድረግ በሰው ሀይል አቅም ግንባታ ላይ ትኩረት ሰጥተው እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተው ከዛሬ ጀምሮ ለሚቀጥሉት አምስት ቀናት የሚሰጠው ፓወር ቢአይ (Power BI) ሶፍት ዌር ስልጠና አንዱ መሆኑን አንስተው የስልጠና ስኬት የሚለካው ስልጠናው ላይ በመሳተፍና በማጠናቀቅ ሳይሆን ከስልጠናው በኋላ ወደ ስራ ክፍላቹ ተመልሳችሁ ከስልጠናው ያገኛቹትን ዕውቀት ተግባራዊ በማድረግ በሚገኘው ውጤትና በየስራ ክፍላቹ ያገኛቹትን ዕውቀት ለሌሎቹ በማስተላለፍ በሚፈጠረው የሰው ሀይል አቅም መሆኑን በመረዳት ስልጠናውን በትኩረትና በትጋት ተከታትለው ተግባራዊ እንዲያደርጉ የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።
ስልጠናውን ኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ከቶኒብሌየር ኢንስቲትዩት ለግሎባል ለውጥ(Tony Blar Institute for Global Chang) ጋር በመተባበር ለሚቀጥሉት አምስት ቀናት የሚሰጥ ሲሆን ከተቋሙ የተለያዩ የስራ ክፍሎች ለተወጣጡ በቁጥር 50 የሚሆኑ ሰልጠኞች በስልጠናው ይሳተፋሉ።










