ስለ ኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት

በሳይንሳዊ ዘዴዎች የተሰበሰቡ እና የተቀናጁ ስታቲስቲካዊ መረጃዎች የአንድን ሀገር ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ዴሞክራሲያዊ ዕድገትና ልማት ለማፋጠን እንዲሁም የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል መሠረታዊ ግብዓቶች ናቸው። እነዚህ መረጃዎች መንግሥትና ሌሎች ተቋማት ለተለያዩ ዘርፎች ፖሊሲዎችን ለመቅረጽ፣ የፖሊሲዎችን አተገባበር ለመከታተልና ለመገምገም፣ እንዲሁም በተጨባጭ መረጃ ላይ የተመሰረቱ የወደፊት ውሳኔዎችን ለመወሰን ያስችላሉ።
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት (ኢ.ስ.አ.) ከናሙና ዳሰሳዎች፣ ከቆጠራዎች እና ከአስተዳደራዊ መዛግብት ከተለያዩ ዘርፎች መረጃዎችን በመሰብሰብ፣ በማቀናጀት፣ በመተንተንና ስታቲስቲካዊ ሪፖርቶችን ለተጠቃሚዎች በማቅረብ ማዕከላዊ ሚና ይጫወታል። በተጨማሪም ለመንግሥት መ/ቤቶች፣ ለተቋማትና ለግለሰቦች ዘመናዊ የአስተዳደራዊ መረጃ መዛግብት፣ የምዝገባ እና የሪፖርት ሥርዓቶችን ለማቋቋም የቴክኒክ መመሪያና ድጋፍ ይሰጣል። እንዲሁም የአስተዳደራዊ መረጃ መዛግብትና የምዝገባ ሥርዓቶችን ለማጠናከር የአሠራር መመሪያዎችና ሙያዊ የምክር አገልግሎቶችን በመስጠት የተቋማትን አቅም ያጎለብታል።
እያደገ የመጣውን የስታቲስቲካዊ መረጃ ፍላጎት ለማሟላትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸውን መስፈርቶችንና ደረጃዎችን ለማሟላት፣ በቀጣይነት የኢ.ስ.አ. በስታቲስቲክስ ጥናት ዘዴዎቹ፣ በመረጃ አሰባሰብ፣ በማቀናበር፣ በምደባ፣ በትንተናና በስርጭት የአሠራር ሂደቶቹን እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀሙን በማሻሻል በተከታታይነት እያጠናከረ ይገኛል።

ተልዕኮ

የተቀናጀ የስታቲስቲክስ አሰራር ስርዓትን በመዘርጋትና በመተግበር፤ ግልጽነትና የሙያ ሥነ-ምግባርን በተከተለ መንገድ ደረጃቸውን የጠበቁ ሳይንሳዊ የሥነ-ጥናት ዘዴዎችንና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ተዓማኒነት ያላቸው ኦፊሴላዊ የስታቲስቲክስ መረጃዎችን ማመንጨት፣ መተንተንና ለተጠቃሚዎች በወቅቱና በአግባቡ ማሰራጨት።

ራዕይ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እና ተዓማኒ የሆነ የኦፊሴላዊ ስታቲስቲክስ የመረጃ ልህቀት ማዕከል ሆኖ ማየት።

እሴቶቻችን

ግልጽነት ፣ ተዓማኒነት ፣ ምስጢር ጠባቂነት ፣ ተጠያቂነት ፣ አካታችነት ፣ ቅንጅት ፣ የሙያ ሥነ-ምግባርና ነጻነት ፣ ትብብርና አጋርነት ፣ ተደራሽነት ፣ ትህትና ፣ የቡድን ሥራ

Institutional (organizational philosophy)

By using scientific methods; we strive to provide quality data for better decision making.