

ጥቅምት 14/02/2018 ዓ.ም አዲስ አበባ፣
የዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት ለኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ለስታቲስቲክስ መረጃን ዝግጅት የሚያግዙ የአይ ቲ (IT) ዕቃዎች ድጋፍ አደረገ።

በርክክብ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ክቡር ዶ/ር በከር ሻሌ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ወቅታዊና ጥራቱን የጠበቀ የስራ ስምሪትና የፍልሰት መረጃዎችን ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች በማሰባሰብና ተንትኖ ጥቅም ላይ ለማዋል እየሰራ መሆኑን ገልፀው ዛሬ በዓለም አቀፍ የስራ ድርጅት የተደረገልን ድጋፍ እየተሰሩ የሚገኙትን ለሪፖርት ዝግጅት ያላቸው አጋዥነት ከፍተኛ መሆኑን አንስተው የዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት (ILO) ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸው በመግለጽ በተቋማቱ መካከል ያለው አጋርነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

በተቋሙ ዋና መስሪያ ቤት ተገኝተው የድጋፉ ርክክብ ያደረጉት የዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት (ILO) የኢትዮጵያ፣ የጅቡቲ፣ የሶማሊያ፣ የሱዳን እና የደቡብ ሱዳን ካንትሪ ዳይሬክተር የሆኑት ሚስተር ካምቡላ ናዳባ ከተቋሙ ጋር የሌበርና ፍልሰት ስታቲስቲክስን ወቅታዊና ጥራቱን የጠበቀ የመረጃ አቅርቦትን ለማሳደግ የተጀመረው አጋርነት ገልፀው በተቋሙ እየተሰሩ የሚገኙ የሪኢኖቬሽን ስራዎችን ጎብኝተዋል።
በድጋፍ የተገኙት የአይ ቲ ዕቃዎች በ2017 ከመስክ መረጃ መሰብሰብ ተግባር የተጠናቀቀው ብሔራዊ የተቀናጀ የቤተሰብ ጥናት የመረጃ ትንተናና ሪፖርት ዝግጅት ስራ እንደሚያግዝ የቤተሰብ በጀትና ሌበር ስታቲስቲክስ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ፉፋ ቡልቶ ገልፀዋል።



