ወርሃዊ የችርቻሮ ዋጋ ጥናት በ1956 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ተጀመረ፡፡ የጥናቱ ሽፋን ከጊዜ ወደ ጊዜ ዕድገት አሳይቷል፡፡ በአሁኑ ጊዜ መረጃ የመሰብሰብ ስራው በ9 ክልሎችና 2 ከተማ አስተዳደሮች ከየዞኑ በተመረጡ 200 ወካይ ከተሞች በመካሄድ ላይ ይገኛል። የችርቻሮ ዋጋ ጥናት 650 የሚሆኑ ዋና ዋና የኢንዱሰትሪና የግብርና ምርቶች ዕቃዎችና አገልግሎቶችን ይሸፍናል፡፡ የሀገሪቱን የልማት ፖሊሲን መሰረት ባደረገ መልኩ የዋጋ ስታቲስቲክስ ስራ ክፍል የዕቃዎች እና አገልግሎቶች ዋጋ ለዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች፣ ለማረሚያ ቤቶች፣ ለወታደርና ፖሊስ ካምፖችና ለሆሰፒታሎች  ለጨረታ ግዥ የሚፈለገው ወርሃዊ የችርቻሮ ዋጋ ጥናትና  ጥራቱን የጠበቀ ስታቲስቲካል ሪፖርት በማመንጨት ለተጠቃሚዎች ያሰራጫል።


አመልካች የሆኑ የዋጋ ኢንዴክሶች (Consumer Price Index) ወርሃዊ የሸማቾች ዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ (CPI) እና የዋጋ ግሽበት (Inflation) ወርሃዊ ፣ አመታዊ እና ተንከባላይ አማካይ (Moving Average) ለፖሊሲ አውጭዎችና ሌሎች አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተጠቃሚዎች ወቅታቸውን ጠብቀው ይሰራጫሉ፡፡


የግብርና ምርቶች አምራች ዋጋ ጥናት በ1973 ዓ.ም የተቀናጀ የቤተሰብ ሰርቬይ ፕሮግራም አካል ሆኖ  (Integrated Household Survey Program) መጠናት ተጀመረ፡፡ መረጃው በገጠር ከሚኖሩ የገበሬ ቤተሰቦችና የግብርና ምርት አምራቾች ህብረት ስራ ማህበራት ይሰበሰባል፡፡ የሚሰበሰበው መረጃ የአምራች ዋጋ ሲሆን 100 ያህል ዋና ዋና የግብርና ምረቶች የተካተቱበት ነው፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ  ¨pq©ና  ጥራቱን  የጠበቀ ወርሃዊ ስታቲስቲካል  የዋጋ መረጃ ተዘጋጅቶ ለተጠቃሚዎች ይሰራጫል። በአሁኑ ጊዜ ጥናቱ በ526 የገጠር ቆጠራ ቦታዎች በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡


የግብርና ምርቶች አምራች ዋጋ ኢንዴክስ የአገሪቱ አርሶ አደሮች ካመረቷቸው የግብርና ምርቶች የሚያገኙትን ገቢ ሁኔታ መለኪያ ለመለካት ያገለግላል፡፡ የግብርና ምርቶች ኢንዴክስና (Producer Price Index) የግብርና ምርቶች አምራች ዋጋ ግሽበት (Producer Price Infilation) በየወሩ ተዘጋጅቶ ለፖሊሲ አውጭዎችና ሌሎች አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተጠቃሚዎች ወቅታቸውን ጠብቀው ይሰራጫሉ፡፡


ወርሃዊ ጥናቱ በአዲስ አበባ ከተማ የሚካሄድ ሲሆን በዋናነት ለመንግስት ግዥ አገልግሎትና ለመንግስት ግዥ ባለስልጣን እንዲሁም ለመግስት መስሪያ ቤቶች የጨረታ ግዥ ስራዎች ግብአት ሆኖ ያገለግላል፡፡ የዋጋ ስታቲስቲክስ ስራ ክፍል ወርሃዊ የጋራ መገልገያ ዕቃዎች የዋጋ ጥናት በማከናወን አስፈላጊው የስታቲስቲክስ መረጃ አዘጋጅቶ ከላይ ስማቸው ለተገለጸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች በወቅቱ እንዲደርሳቸው ያደርጋል፡፡


ለአፍሪካ የጋራ መገበያያ ገንዘብ ለመፍጠር እና የማክሮ ኢኮኖሚ ውህዳት ለማምጣት ለምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ሀገራት የጋራ ገበያ ድርጅት የዋጋ ኢንዴክስና የዋጋ ግሽበት መረጃ ለደቡብና ምስራቅ የጋራ ገበያ ሀገራት (ኮሜሳ) ተዘጋጅቶ በየወሩ ይላካል፡፡