
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ከአስተዳደራዊ መዛግብት የሚገኙ መረጃዎችን እንደኦፊሴላዊ ስታቲስቲክስ መረጃ ለመጠቀም የሚያግዝ የአቅም ግንባታ ስልጠና በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ከተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ለተውጣጡ አመራሮችና ባለሙያዎች በክልሉ ዋና ከተማ ሰመራ እየተሰጠ ይገኛል።

ስልጠናው ያስጀመሩት የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ ክቡር አቶ አሊ መሀመድ በክልሉ የተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የሚያመነጩትን የአስተዳደራዊ መረጃዎችን አሰባሰብ፣ አያያዝ፣አደረጃጀትና ትንተና ሂደቱን በማሻሻል እንደኦፊሴላዊ ስታቲስቲክስ መረጃ ለመጠቀም ስለመረጃዎቹ አስፈላጊነትና ያላቸው ጠቀሜታ ላይ በቂ ግንዛቤና መሠረታዊ ዕውቀት ያለው አመራርና ባለሙያ መፍጠር ቀዳሚ ተግባር እንደሆነ አንስተው ስልጠናው ከዚህ አንፃር የሚታያውን የሰው ሀይል የአቅም ክፍተቶችን በማሻሻል ከክልሉ የተለያዩ ሴክተር መሠሪያ ቤቶች የሚያመነጩትን የአስተዳደራዊ መረጃዎችን ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕቅዶች ግብዓትነት ለመጠቀም የሚያስችል የባለሙያዎችን አቅም ለመፍጠር የተዘጋጀ ስልጠና መሆኑን አስረድተው የስልጠናው ተሳታፊዎች ወደየሴክተር መስሪያ ቤታቸው ሲመለሱ ያገኙትን እውቀትና ልምድ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጠባቅበቸውም መልዕክታቸውን አሰተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የስታቲስቲክስ ሜቶዶሎጂና ልማት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬከተር ክብርት ወ/ሮ ጀሚላ መሀመድ ስልጠናው በየሴከተሩ ያለውን የአስተዳደራዊ መረጃ አያያዝ ለማሻሻል የሚረዱ የስታቲስቲክ ፅንሰ ሀሳብና የቴክኖሎጂ አጠቀቃም ላይ በየክልሉ የሚገኙትን ባለሙያዎች አቅም በማሳደግ ከአስተዳደራዊ መዛግብት የሚገኙትን መረጃዎችን ጥራት በማሻሻል እንደአንድ ኦፊሴላዊ ስታቲስቲክስ መረጃ ለመጠቀም በተቋሙ ሪፎርም ትኩረት ተሰጥቶ በየክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙት ተግባራት አካል እንደሆነ ገልፀዋል።

ስልጠናው በአስተዳደር መረጃዎች አመዘጋገብ፣አያያዝና የቴክኖሎጂ አጠቀቃም ላይ ለቀጣይ ሶስት ቀናት እንደሚሰጥ ከስልጠናው መርሀግብር ለመረዳት ተችሏል።

