ሐምሌ 2/2017ዓ.ም አዲስ አበባ፣

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት እያካሄደ በሚገኘው የግብርና ቆጠራ አፈፃፀምና ቀጣይ ስራዎች ላይ ከባለድርሻ አካካት ጋር ውይይት አደረገ።

በውይይት መድረኩ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የተቋሙ የኢኮኖሚ ስታቲስቲክስ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን ቀሬ የግብርና ቆጠራን በሚመለከት ከቆጠራው ቅድመ ዝግጅት ተግባራት አሁን እስክደረሰበት የስራው አፈፃፀም ድረስ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ከፍተኛ ሚና እንዳለው አንስተው የዛሬው መድረክም ስራው የደረሰበትን አፈፃፀምና ቀጣይ ቀሪ ስራዎች ለመወያየት እንደሆነ ገልፀዋል።

የግብርና ቆጠራ አጠቃላይ ሂደትና የደረሰበትን አፈፃፀም የሚያሳይ ገለፃ የቀረበ ሲሆን በቀረበው ገለፃና በቀጣይ የበልግ፣ የንግድ እርሻዎች መረጃ መሰብሰብና የሪፖርት ዝግጅት ተግባራት ላይ ውይይት ተደርጎበታል። በመድረኩ የተገኙት ባለድርሻ አካላትም ቆጠራው ጥሩ የሚባል አፈፃፀም ላይ መሆኑን ከቀረበው ሪፖርት መረዳታቸውን ተናግረዋል።

በመድረኩ ማጠቃለያ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ክቡር ዶ/ር በከር ሻሌ በመድረኩ ለተገኙት ባለድርሻ አካላት ከቆጠራው ቅድመ ዝግጅት አሁን እስከደረሰበት አፈፃፀም ላደረጉት ተሳትፎ አመስግነው፤ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በጋራ መስራት ውጤታማ እንደሚያደርግ በማንሳት ቀጣይ ቀሪ ስራዎችንም በጋራ እንደሚሰሩ ገልፀው የውይይት መደረኩ ተጠናቋል።
