ግንቦት 21/2017ዓ.ም አዲስ አበባ፣

በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ከ2015−2017ዓ.ም በተቋሙ ዋና መስሪያ ቤት የተከናወኑ ዋና ዋና የሪፎርም ለውጥ ስራዎች በተመለከተ የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ በክቡር አቶ ደሳለኝ ወዳጆ የተመራ ቡድን የስራ ጉብኝት አደረገ።

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ክቡር ዶ/ር በከር ሻሌ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈው ተቋሙ በቋሚ ኮሚቴው ከዚህ በፊት ሲጎበኝ የሰጣቸውን አስተያየቶች እንደግብዓት በመውሰድ የሰራቸውን የለውጥ ስራዎች ለማሳየት የተዘጋጀ መሆኑን ገልፀዋል።

ተቋሙ ከ2015−2017ዓ.ም በሪፎርም ያከናወናቸው ዋና ዋና ለውጦች የተቋሙ መዋቅራዊ አደረጃጀት፣ የሰው ሀይል አቅም ግንባታ፣ ምቹ የስራ ከባቢ መፍጠር፣ የጥናት ስነ−ዘዴዎችን ማሻሻልና ሌሎች ሰፊ የመረጃ ልማት ስራዎች የደረሱበት ደረጃ በተመለከተ በስትራቴጂክ ጉዳዮች ስራ አስፈፃሚ አቶ ሁሴን አጎናፍር ሪፖርት ቀርቧል።

የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጆ እና አባላት ተቋሙን ከዚህ ቀደም ሲጎበኙ በጣም ብዙ ክፍተቶች የነበረበት መሆኑን አንስተው ዛሬ በመስክ ምልከታው ወቅት የታዩትን መሻሻሎች በማድነቅ ይህ በጎ ለውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና ለመረጃ ጥራት ከፍተኛ ድርሻ ያላቸውን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችንም በዚሁ መልኩ የተሻሉ እንዲሆኑ ለማድረግ ትኩረት እንዲሰጥ አስገንዝቧል::

