ህዳር 2/2018ዓ.ም ሚዛን፣

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ከUNFPA ጋር በመተባበር በሚዛን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የተቀናጀ የመረጃ አስተዳደር ሲስተም (IMIS) ላይ ከክልሉ ለተውጣጡ የፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል።

በመድረኩ መክፈቻ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት የፕላንና ልማት ቢሮ ምክትልና የልማት መረጃ ሥ/ሥነ ህዝብ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሰለሞን አየለ እንደገለፁት መረጃዎች ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ በመሰብሰብና በማጥናት ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትና ዕድገት ማዋል እንዲሁም የተቀናጀ የመረጃ ስርዓትን በመዘርጋትና ወደመረጃ ቋት እንዲገቡና ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ በክልሉ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ሚዛን ቅ/ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሽመልስ ማጅቶ እንደገለፁት የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ባለፉት 60 ዓመታት መረጃዎችን አደራጅቶ በማቅረብ በርካታ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልፀው፤ በአንድ የመረጃ ቋት የሚተዳደር የተቀናጀ የመረጃ አስተዳደር ያለው ተቋም መሆኑን ተናግረዋል። ክልሉ ከተደራጀ ወዲህ መረጃዎችን በራሱ የመረጃ ቋት እንዲይዝ በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውንም አክለው ተናግረዋል።

በመድረኩ የለማው የተቀናጀ የመረጃ አስተዳደር ሲስተም ዳታ ቤዝ የማስተዋወቅና ተያያዥ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል።

መድረኩ በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ፣ UNFPA እና በክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ በጋራ መዘጋጀቱ ተገልጿል።

