ጥር 17/2018 ዓ.ም አዳማ፣

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት በመካከለኛው ዘመን (2016 – 2018 ዓ.ም) የስታቲስቲክስ ልማት ስትራቴጂክ ዕቅድ ክንውን ላይ ከተወካዮች የምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በአዳማ ከተማ ውይይት አካሄደ።

በመድረኩ ተገኝተው ስልጠናውን ያስጀመሩት የተከበሩ አቶ ደሳለኝ ወዳጀ ተቋሙ ላለፉት ስድስት አስርት አመታት ለሀገሪቱ ልማት ዕቅድ ፖሊሲና ስትራቴጂ ለማዘጋጀት የሚያስፈልጉትን መረጃዎች በማቅረብ በየዘመኑ በሀገራችን ለተመዘገቡ የልማት ዕድገት የራሱን ደማቅ አሻራ እያበረከተ የሚገኝ አንጋፋ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የስታቲስቲክስ መረጃ ለሀገራችን ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና የዜጎች ፍትሀዊ ተጠቃሚኒነት የተረጋገጠበት ሀገር ለመገንባት የማይተካ ሚና እንዳለው ያስረዱት የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በረከት ፍስሀፅዮን መንግስት ይህንን ተረድቶ በሀገሪቱ ጠንካራ የስታቲስቲክስ ተቋም እንዲኖር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተቋሙ በመካከለኛ ዘመን (2016 – 2018 ዓ.ም) የስታቲስቲክስ ልማት ስትራቴጂ የእስከ አሁን አፈጻጸሙ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር በከር ሻሌ የተከበሩ የህዝብ ተወዮች ምክር ቤት ቋሚ አባላትና አመራሮች በተቋማችን እየተሰሩ የሚገኙት ስራዎች ላይ ለመወያየትና ለመደጋፍ ጥሪያችንን አክብሮ በመገኘታቸው ያላቸውን ምስጋና አቅርበው በተከበሩት የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አባላት የተነሱትን ገንቢ ሀሳቦች በመውሰድ በቀጣይ በሚከናወኑ ቀሪ የበጀት ዓመቱ ተግባራት በማካተት ተግባራዊ እንደሚደረጉ ገልጸዋል።

የውይይት መድረኩን የመሩት በተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ የተከበሩ ወ/ሮ መሠረት ሀይሌ ውይይቱ ስለተቋሙ ያላቸውን ግንዛቤ እንዳሳደገላቸው በማንሳት ተቋሙ ከዚህ በተሻለ ሀገርን የማገልገል አቅም እንዲኖረው የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አባላት አስፈላገውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡



