
የካቲት 29/2018 ዓ.ም ሲዳማ፣
በክረምት 2018 ዓ.ም የበጎ አድራጎት በሲዳማ ክልላዊ መንግስት ደቡብ ሲዳማ ዞን ዳራ ወረዳ መጬሾ ቀበሌ በፕላንና ልማት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የገጠር መኖሪያ ቤቶች ሞዴል የተሰሩ መኖሪያ ቤቶች የፕላንና ልማት ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ፍፁም አሰፋና የተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ተመርቆ ለተጠቃሚዎች ተሰጥቷል።

በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ፍፁም አሰፋ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸውና ተጠሪ ተቋማቱ ባለፉት አራት ዓመታት ሰራተኞችን በማስተባበርና ከተመደበላቸው ጥቂት በጀት በመቀነስ በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች የሚገኙ የአቅመ ደካማ ቤተሰቦች ቤቶች በመገንባት፣ የተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ በክረምት በጎ አድራጎት ስራ በመሳተፍ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ሲወጣ መቆየቱን ጠቅሰው ባለፈው ዓመት ክረምት በሲዳማ ክልል ተጀምረው ዛሬ የተመረቁት ቤቶች በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን የገጠር ህዝቦችን የአኗኗር ዘይቤ ለመለወጥ ታስበው በተጀመሩት የገጠር መኖሪያ ቤቶች ሞዴል መሰረት አድርገው የተሰሩ መሆናቸው ልዩ እንደሚያደርጋቸው ገልፀዋል። ሚኒስትሯ አክለውም የክልሉ አመራር እነዚህ የተሰሩ ሞዴል ቤቶችን እንደ ናሙና በመውሰድና በማስፋፋት የክልሉን የገጠር ህዝብ አኗኗር ለማሻሻል መስራት እንደሚጠበቅባቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የሲዳማ ክልል ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ደስታ ሌዳሞ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ተጠሪ ተቋማቱ በክልላቸው በክረምት በጎ አድራጎት በሰሩት የገጠር መኖሪያ ቤቶች ሞዴል መኖሪያ ቤቶች ምስጋና አቅርበው ዛሬ የተመረቁት ቤቶች ክልሉ በቀጣይ የገጠር ነዋሪዎች አኗኗር ለማሻሻል ለሚሰራቸው ስራዎች እነደሚጠቀሙ ገልፀው በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና በተጠሪ ተቋማቱ የተጀመሩትን ስራ በማስፋፋት የክልሉ የገጠር ህዝብ አኗኗር ለማሻሻል በትጋት እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

ቤቶቹን የተረከቡት ነዋሪዎች የተሰሩት ቤቶች ለኑሮ የሚያስፈልጋቸውን መሰረተ ልማቶችና ግብዓቶች ያሟሉና ምቹ በመሆናቸው አኗኗራቸው ላይ ከፍተኛ ለውጥ የሚያመጡ መሆኑን ገልፀው ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ተጠሪ ተቋማቱ አመራሮችና ሰራተኞች ላደረጉላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።






