
ሐምሌ 28/2017ዓ.ም አዳማ፣
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት በየዓመቱ ከሚያካሂዳቸው የናሙና ጥናቶች አንዱ የሆነውን የ2018ዓ.ም ግብርና ናሙና ጥናት የመስክ ስራ የሚሰሩትን መረጃ ሰብሳቢዎች የሚያሰለጥኑ አሰልጣኞች ስልጠና መሰጠት ተጀመረ።


በስልጠናው መክፈቻ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ክቡር ዶ/ር በከር ሻሌ የ2018ዓ.ም የግብርና ናሙና ጥናትን ከሁለተኛ ዙር ሀገር አቀፍ የግብርና ቆጠራ የመስክ ስራ በሚጠናቀቅበት ማግስት ማካሄድ ያስፈለገው በጥናቱ የሁለተኛ ዙር የግብርና ቆጠራ ውጤትን ለመገምገም (validate) ለማድረግ ፣ የግብርና ሴክተር መረጃዎችን ሳይቆራረጡ (Time series) በመጠበቅ በቀጣይነት በማደራጀት ለዘርፉ እቅድና ምርምር ለማዋል፣ ዓመታዊ የሀገሪቱን የእደገት ምጣኔ ለማስላት፣ በምርት ዘመኑ የሚኖረውን የሰብል ምርትና የእንስሳት ሀብት እድገትን በማወቅ ለመንግስት በምርት እጥረትና ትርፍ ምርት በመመረቱ ምክንያት የሚፈጠሩትን ተፅዕኖዎች ለመቀነስ የሚያስችል መረጃ ቀድሞ ለመስጠት ጥናቱን ማካሄድ አስፈላጊ መሆኑን አንስተው በስልጠናው የሚሳተፉ ሰልጣኞች ዓመቱን በሙሉ ሲካሄድ ከቆየው የሁለተኛ ዙር የግብርና ቆጠራ በተለያየ ደረጃ በነበራችሁ ተሳትፎ የተገኙትን ጠቃሚ ልምዶችና እንደክፍተት የታዩ ጉዳዮችን በስልጠናችሁ ወቅት በመወያየትና ልምድ በማጋራት ቀጣይ በመስክ ስራው ለሚሳተፈው የሰው ሀይል የተሟላ ስልጠና ለመስጠት የሚያስችል እውቀትና ልምድ ለመጨበጥ ስልጠናውን በትኩረት መሳተፍ እንደሚገባቸው መመሪያ በመስጠት ስልጠናውን አስጀምረዋል።


የግብርና ስታቲስቲክስ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ አብዱላዚዝ ሽፋ ስለጥናቱ አጠቃላይ ገለፃ በመስጠት ስልጠናው ለሚቀጥሉት 10 ቀናት በጥናቱ ጽንሰ ሀሳብ፣ ስለጥናቱ ስነ ዘዴ፣ መጠይቆችና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ከ26ቱ የተቋሙ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ለተውጣጡ ስታቲስቲሺያን እንደሚሰጥ ገልፀዋል።

