
ጥቅምት25/2018 ዓ.ም
የፕላንና ልማት ሚኒስትርና የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት በጋራ ባዘጋጁት ብሔራዊ ስታቲስቲክስ ስርዓት ረቂቅ አዋጅ ላይ የክልልና የከተማ አስተዳደር የፕላንና ልማት ቢሮ የስራ ኃላፊዎችና ከፍተኛ ባለሙያዎች በቢሾፍቱ ከተማ ከጥቅምት 24-25/2018 ዓ.ም ውይይት አደረጉ።

በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ተገኝተው ውይይቱን ያስጀመሩት የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ኤቢሳ አሰፋ በየጊዜው እያደገ የመጣውን ሳይንሳዊ የስታቲስቲክስ መረጃ ፍላጎት ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በሚያሳትፈው የብሄራዊ ስታቲስቲክስ ስርዓት ጥላ ስር በተሟላ መልኩ ለመመለስ ከሀገራችንና አለም አቀፍ መሰረታዊ ህጎች ጋር የሚናበብ ብሄራዊ የስታቲስቲክስ ስርዓት የሚመራበት የህግ ማዕቀፍ ማዘጋጀትና ተግባራዊ ማድረግ ለሀገራዊ ስታቲስቲክስ ዘርፍ ልማት ስኬታማነት ከሚያስፈልጉ መሰረታዊ ጉዳዮች አንዱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አቶ አብነት ሐዋዝ የዋና ዳይሬክተር ጽ/ቤት ኃላፊ የክልልና ከተማ አስተዳደር ፕላንና ልማት ቢሮ አሁን ለውይይት የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በሀሳብ ከማዳበር በተጨማሪ በቀጣይ አዋጁ ተግባራዊ ሲደረግም ያላቸው ድርሻና ተጠቃሚነት የጎላ መሆኑን በመረዳት የተሟላ ሀሳብ በመስጠት የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ማዳበር እንደሚጠበቅባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል ፡፡


ተሳታፊዎች የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ለሀገራችን የስታቲስቲክስ ስርዓት ዕድገት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አንስተው ረቂቅ አዋጁ ዳብሮ ስራ ላይ ሲውል ሀገራችን ወጥና ተመጋጋቢ የሆነ የመረጃ ስርዓትና ፍሰት እንዲኖራት ከማስቻል አንጻር የአዋጁ ሚና የጎላ መሆኑን ገልፀዋል።


ከ12ቱ ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ ፕላንና ልማት ቢሮ የተውጣጡ የቢሮ ሀላፊዎችና ባለሙያዎች በአጠቃላይ 40 ሰዎች በውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል።

