ታህሳስ 18/2018 ዓ.ም አዳማ
ለምዕራፍ ሁለት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ የቅድመ አሰልጣኞች ስልጠና ከተቋሙ ዋና መስሪያ ቤትና ከ26ቱ ቅ/ጽ/ቤት ለተወጣጡ የስራ ኃላፊዎችና ከፍተኛ ባለሙያዎች በአዳማ ከተማ እየተሰጠ ይገኛል።

በስልጠናው የመክፈቻ መድረክ ላይ የተገኙት የተቋሙ የስታቲስቲክስ ዲጂታላይዜሽን ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር ክብርት ዶክተር ሜሮን ክፈለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ የመጀመሪያ ምዕራፍ የመስክ ስራ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ በትጋት ለሰሩትና ድጋፍ ላደረጉት ለተቋሙ የዋና መስሪያ ቤትና የቅርጫፍ ጽህፈት ቤት አመራሮች፣የቢዝነስ ስታቲስቲክስ ስራ ክፍል ባለሙያዎች፣የመስክ ስራ አስተባባሪዎች፣ ተቆጣጣሪዎችና መረጃ ሰብሳቢዎች እንዲሁም በመላ ሀገሪቱ በየደረጃው ለሚገኙት የመንግስት አደረጃጀቶችና ለመረጃ ሰጪዎች ያላቸውን ምስጋና አቅርበዋል። በተጨማሪም ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ የቆጠራው ወሳኝ ምዕራፍ የሆነውን ሁለተኛ ዙር የቆጠራ የመስክ ስራ ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት ሲደረግ በዓመቱ በቀጣይ ወራት እንደሀገር የሚኖሩትን ታላላቅ ሀገራዊ ሁነቶች በስራው ላይ የሚኖራቸውን ተጽዕኖ ታሳቢ በማድረግ፤ በመጀመሪያ ዙር ክንውን አፈጻጸም ወቅት የተገኙትን ጥሩ ተሞክሮዎችን አጠናክሮ በመቀጠልና የታዩትን ክፍተቶች በማረም ስራውን በአጠረ ጊዜ ለማጠናቀቅ መታሰቡን አንስተው በመጀመሪያ ዙር የታየው ትጋትና ትብብር ቀጣይ ቀሪ የቆጠራውን ስራ በስኬት ለማጠናቀቅ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ መልዕክት በማስተላለፍ የቅድመ አሰልጣኞች ስልጠና ተሳታፊዎች በቀጣይ ለቆጠራው የመስክ ስራ የሚያስፈልገው የሰው ሀይል የሚያሰነጥኑ ብቁ አሰልጣኞች ለማፍራት ስልጠናው በሙሉ ትኩረት እንዲከታተሉ የስራ መመሪያ በመስጠት ስልጠናውን አስጀምረዋል።

ስልጠናው ለሚቀጥሉት አስር ቀናት በቆጠራው የመስክ ስራ ሜቶዶሎጅ፣ ጽንሰ ሀሳብና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ በማተኮር እንደሚሰጥ ከመረሀ-ግብሩ ለማወቅ ተችሏል።




