የሁለተኛ ዙር የግብርና ቆጠራን በሚመለከት ለክልሉ አመራር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ

ታህሳስ 25/04/2017 ዓ.ም፣ የአትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ለአፉር ክልል ከፍተኛ፣ መካከለኛና የወረዳ አመራሮች የሁለተኛ ዙር የግብርና ቆጠራ አስፈላጊነት፣ ጠቀሜታና በክልሉ በመስክ መረጃ የመሰብሰብ ተግባራት ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በሰመራ ከተማ ተሰጠ።

በስልጠና መድረኩ ላይ ተገኝተው ስለመድረኩ ዓላማ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በከር ሻሌ የሁለተኛ ዙር የግብርና ቆጠራ በሀገራችን ከሃያ ሁለት ዓመታት በኋላ እያተካሄደ የሚገኝና በሚያስገኘውም መረጃ ለአፉር ክልልም ሆነ ለሀገራችን ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተው ፤ የዚህ መድረክ ዓላማ የክልሉ አመራር የቆጠራው ስራ የራሱ ቁልፍ የልማት ተግባር መሆኑን ተገንዝቦ ለስኬታማነቱ አስፈላጊውን ትኩረት ሰጥቶ እንዲደግፍ የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር እንደሆነ ገልፀው የክልሉ ክቡር ፕሬዘዳንት ሀጂ አወል አርባ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው ይህ መድረክ በዚህ ደረጃ እንዲዘጋጅ በማድረጋቸው ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።

ስለቆጠራው ምንነት፣አስፈላጊነትና ጠቀሜታ እንዲሁም በክልሉ የእስካሁኑ የቆጠራው የመስክ ተግባራት አፈፃፀም ያለበትን ሁኔታ በሚመለከት የተዘጋጀ ገላጻ በተቋሙ ምትክል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ጀሚላ መሀመድ ቀርቦ ግንዛቤ የተፈጠረበት ሲሆን ውይይትም ተደርጎበታል።

የክልሉ ፕሬዘዳንት ክቡር ሀጂ አዋል አርባ የተቋሙ ከፍተኛ አመራር በክልላችን እየተካሄደ ስለሚገኘው ሁለተኛ ዙር የግብርና ቆጠራ ምንነት፣አስፈላጊነትና ጠቀሜታ እንዲሁም በክልሉ የእስካሁኑ የቆጠራው የመስክ ተግባራት አፈጸጻም ያለበት ሁኔታ አመራሩ ማወቅ አለበት ብሎ ትኩረት ሰጥቶ በመሃላቸው በመገኘት ለተሰጣቸው ግንዛቤ ምስጋና አቅርበው ክልሉ ያለውን እምቅ የእርሻ ልማትና የእንስሳት ሀብት አቅም ጥራት ባለው የስታቲስቲክስ መረጃ ተለይቶ ካልታወቀ በስተቀር በዘርፉ የሚፈለገውን ልማት እውን ማድረግ እንደማይቻል አመራሩ ተረድቶ የቆጠራውን ቀሪ ተግባራት የዕለት ተዕለት ዕቅዱ አካል አድርጎ በመውሰድ በከፍተኛ ሀላፊነት መምራት እንደሚጠበቅባቸው የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።