የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ከኖርዌይ የስታቲስቲክስ ጋር በመተባበር የተቋሙ የመረጃ ስርጭት ይዘትና ተደራሽነትን ማሻሻል የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ስልጠና ከህዳር 9-13/2017 ዓ.ም በዋና መስሪያ ቤት ተሰጠ።
ስልጠናው ከኖርዌይ ስታቲስቲክስ በመጡትና በኮሙዩኒኬሽን የመረጃ ስርጭት ይዘት ዝግጅት ላይ ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች የተሰጠ ሲሆን በስልጠናው ስታቲስቲክስ መረጃዎችን በተሻለ ይዘትና ቀላል በሆነ መልኩ ለተጠቃሚዎች ማድረስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያላቸውን ልምድና ዕውቀት በስልጠናው ለተሳተፉት ለኮሙዩኒኬሽን፣ ለመረጃ ስርጭትና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አመራሮችና ከፍተኛ ባለሙያዎች አካፍለዋል።
በስልጠናው መዝጊያ ላይ የተገኙት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር በከር ሻሌ ስልጠናው በድረ ገጽ በኩል ወደ ተጠቃሚዎች የሚደርሱትን መርጃዎች ይዘት የተሻለ ለማድረግ ለሚሰሩ ስራዎች ጥሩ አቅም እንደሚፈጥር አንስተው ተሳታፊዎች በስልጠናው ባገኙት ግንዛቤና ልምድ የተሻለ የአርቲክል ይዘትና የመረጃ ተደራሽነትን ለማሻሻል መስራት እንደሚገባቸው በማስረዳት የስታቲስቲክስ ኖርዊይ ለተቋሙ ለሚያደርገው ድጋፍ ምስጋናቸውን በማቅረብ ከተቋሙጋር ያለው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።



