ታህሳስ 01/2018 ዓ.ም አዳማ

ከኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና መስሪያ ቤት ከተለየዩ የስራ ክፍል ለተወጣጡት ሴት ሰራተኞች የስራ ላይ ብቃትና ክህሎት ለማሻሻል የሚያግዝ ስልጠና በአዳማ ከተማ እየተሰጠ ይገኛል።

የተቋሙ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች አካትቶ ትግበራ ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ አዚዛ እስማኤል የተቋሙን ሴት ሰራተኞች ስራን የመፈጸም ብቃትና ክህሎት ለማሳደግ የሚያግዙ የስራ ላይ ስልጠናዎችን በማዘጋጀትና ተግባራዊ በማድረግ የተቋሙ ሴት ሰራተኞች በተሰማሩበት የስራ መስክ ውጤታማ እንዲሆኑ የስራ ክፍላቸው አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝ አንስተው ከዛሬ ጀምሮ ለሚቀጥሉት ሶስት ቀናት የሚሰጠው ስልጠናም ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን ገልፀዋል።

በመድረኩ ተገኝተው ስልጠናውን ያስጀመሩት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብነት ሐዋዝ ተቋሙ ባለፋት ሶስት ዓመታት ተግባራዊ እያደረገ በሚገኘው ተቋማዊ ሪፎርም አንዱና ዋነኛው ትኩረት የሰው ሀይልን የመፈፀም ብቃትና ክህሎት ቀጣይነት ባለው መልኩ ማሻሻል እንደሆነ ገልፀው በተለይም የተቋሙን ሴት ሰራተኞች ሁለንተናዊ የመፈጸም አቅማቸውን በማሳደግ ወደ አመራርነት እንዲመጡ እየተሠራ መሆኑን በማስረዳት ሰልጣኞች ስልጠናውን በትኩረት በመከታተል ለቀጣይ ስራቸው የሚያግዛቸውን ዕውቀትና ክህሎት መቅሰም እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

ስልጠናው ለሚቀጥሉት ሶስት ቀናት በተለያዩ ርዕሶች ላይ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በመጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች ይሰጣል።

