
ታህሳስ 20/2018 ዓ.ም አዳማ፣
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የአስተዳደራዊ መረጃዎች ለኦፊሺያል ስታቲስቲክስ መጠቀም የሚያስችል የመረጃ አያያዝ፣ ጥራትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከኦሮሚያ ፕላንና ልማት ኮሚሽን ለተውጣጡ አመራሮችና ከፍተኛ ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።

የስልጠናውን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የተቋሙ የስታቲስቲክስ ልማትና ሜቶዶሎጂ ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ጀሚላ መሀመድ ተቋሙ ቆጠራን፣ ጥናቶችንና አሰተዳደራዊ መረጃዎችን ለመረጃ ምንጭ እንደሚጠቀም አንስተው በተለያዩ ተቋማት የሚመዘገቡ መረጃዎች አያያዝ፣ ጥራትና አመዘጋገብ ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ በማድረግ ለኦፊሺያል ስታቲስቲክስ ለመጠቀምና የመረጃ ጥራትን ለማሻሻል ስልጠናው መዘጋጀቱን ገልፀዋል። ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም የመረጃ ጥራት ያለውን ጠቀሜታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ስልጠናውን በትኩረት እንዲከታተሉ ለስልጠናው ተሳታፊዎች መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመድረኩ የተገኙት የኦሮሚያ የፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ዩያ ይህ ስልጠና በተቋማት መካከል የሚታየውን የመረጃ አያያዝ፣ አመዘጋገብና ጥራት ችግር ለመፍታት ወሳኝ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ መሆኑን ገልፀው በክልሉ እየተካሄዱ ያሉ ተግባራት በመረጃ ላይ የተመሰረቱ፣ ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ በአለም አቀፍ ደረጃ ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ለማድረግ እንደሆነ ገልፀዋል። የስልጠናው ተሳታፊዎችም ስልጠናውን በትኩረት በመሰልጠን ያገኛችሁትን እውቀትና ግንዛቤ ወደስራ ገበታችሁ ስትመለሱ ተግባራዊ እንድታደርጉ ሲሉ አሳስበዋል።

ስልጠናው በመረጃ ጥራት ፅንሰ ሀሳብ፣ የመረጃ ጥራት ስታንዳርድ፣ ወቅታዊነት፣ የመረጃ ጥራት ተግዳሮቶች፣ የአስተዳደራዊ መረጃ አያያዝና አመዘጋገብ፤ ለመረጃ መሰብሰብ፣ ማጠናቀርና ትንተና ጥቅም ላይ የሚውሉ ሶፍትዌሮች፣ የመረጃ ማከማቻና ስርጭት እንዲሁም የመረጃ ሚስጥራዊነት ላይ ባተኮሩ ርዕሶች ላይ ለቀጣይ አምስት ቀናት እንደሚሰጥ ከወጣው መርሀ ግብር ለመረዳት ተችሏል።





