ሰኔ5/2017ዓ.ም ሀዋሳ፣
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የአስተዳደራዊ መረጃ አመዘጋገብ፣ አያያዝና ትንተና ለማሻሻል የሚያስችል ስልጠና ለሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕላንና ልማት ቢሮ ሀላፊዎችና ባለሙያዎች ሰጠ።

በስልጠናውን መክፈቻ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የስታቲስቲክስ ልማትና ሜቶዶሎጂ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ጀሚላ መሀመድ የአስተዳደራዊ መዛግብት መረጃዎች ለስታቲስቲክስ መረጃ ግብዓት መሆናቸውን አንስተው እንደሀገር ያሉትን የመረጃ ክፍተቶች ለመሙላትና የክልሎችን አካውንት ለማዘጋጀት አስተዳደራዊ መረጃዎች ለኦፊሴላዊ ስታቲስቲክስ ምንጭ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው ገልፀዋል። ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም የስልጠናው ዋና ዓላማ አስተዳደራዊ መረጃዎች ለሀገራዊ እና ክልላዊ ስታቲስቲክስ ምርት ያላቸውን አጠቃቀም ለማሳደግ የስታቲስቲክስ ሴክተር አመራሩንና ባለሙያውን በእውቀትና በክህሎት ለማብቃት ነውሲሉ ገልፀዋል።

በመድረኩ የተገኙት የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የፕላንና ልማት ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር አራርሶ ገረመው መረጃ ለእቅድ ዝግጅት፣ ፖሊሲ ለማውጣት ወሳኝ በመሆኑ ወቅታዊ፣ ተነፃፃሪና ጥራት ያለው የአስተዳደራዊ መረጃ አመዘጋገብና አያያዝ አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት የዛሬው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መዘጋጀቱን ገልፀዋል።

ስልጠናው በስታቲስቲክስ ፅንሰ ሀሳብ፣ የመረጃ አመዘጋገብ ዘዴዎች፣ አያያዝና ትንተና ፣ የመረጃ ጥራት፣ የመረጃ ቅብብሎሽ፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣የመረጃ ቋት አደረጃጀት፣ መረጃ ለመተንተን የሚረዱ ሶፍትዌሮችና የስታቲስቲክስ ህግ ያተኮሩ ርዕሶች ላይ በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የአስተዳደር መረጃ ቅንጅት ፣ስታንደርድና ጥራት መሪ ስራ አስፈፃሚ ከፍተኛ ባለሙያዎች ከሲዳማ ብሔራዊ ክልል፣ ከአራቱ የሲዳማ ዞኖች፣ ከሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ለተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች እየተሰጠ ይገኛል።


