
ነሐሴ 7/2017ዓ.ም አዲስ አበባ፣

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት በ2018ዓ.ም ለሚካያሂደው የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ሁለተኛ ዙር የአሰልጣኖች ስልጠና በ13 የስልጠና ማዕከላት መሰጠት ተጀመረ።

ስልጠናውን ከዋናው መስሪያ ቤት በበይነ መረብ ያስጀመሩት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ክቡር ዶ/ር በከር ሻሌ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት በመካከለኛ ዘመን የስታቲስቲክስ ልማት ፕሮግራም ለማከናወን ካቀዳቸው ጥናቶችና ቆጠራዎች መካከል በ2017ዓ.ም ሁለት ጥናቶችና የግብርና ቆጠራ በተለየ ትኩረትና ትጋት ውጤታማ ስራ መስራት መቻሉን ገልፀው ይህ ስኬት ሊገኝ የቻለው በመላው የሀገራችን ህዝቦች፣ የየአካባቢው የመንግስት የስራ ሀላፊዎች፣ የተቋማችን ሰራተኞችና መረጃ ሰብሳቢዎች ባደረጉት ድጋፍና ከፍተኛ ትጋት በመሆኑ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። የስታቲስቲክስ ልማት ፕሮግራም አካል የሆነው የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራን ለማካሄድ ስንዘጋጅ ባለፈው ዓመት በሰራናቸው ትላልቅ ስራዎች ያገኘናቸውን ጠቃሚ ተሞክሮዎች አካተን በቂ ዝግጅት ለማድረግ ጥረት የተደረገ ቢሆንም የቆጠራውን ስራ ስኬታማ ለማድረግ የሰው ሀይል ያለውን የማይተካ ሚና በመገንዘብ የዛሬው ሰልጣኞች የነገ አሰልጣኞች በቀጣይ ለምታሰለጥኑት የሰው ሀይል የተሟላ ዕውቀት፣ ልምድና ክህሎት ለማስጨበጥ በስልጠናው የሚሰጣችሁን የጽንሰ ሀሳብ፣ የተግባር ልምምድና ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በተሟላ መልኩ መከታተልና መረዳት እንደሚጠበቅባቸው መልዕክት በማስተላለፍ ስልጠናውን አስጀምረዋል።


ከቆጠራው የሚገኘው መረጃ በሀገራችን የኢኮኖሚ ዘርፉን ለማሳግደግ ለሚዘጋጁ ዕቅድ፣ ፖሊሲና ስትራቴጂ እንዲሁም ብሔራዊ የእድገት ምጣኔን ለማስላት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ያነሱት የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የስታቲስቲክስ ሲስተም ልማትና ሜቶዶሎጂ ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ጀሚላ መሀመድ ይህ ስልጠና በተሟላ መልኩ እንዲጀመር ለሰሩ የዋናው መስሪያ ቤት ባለሙያዎችና የ13ቱ ማዕከላት አስተባባሪዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ስልጠናው በ13 የስልጠና ማዕከላት ከነሐሴ 7/2017ዓ.ም ጀምሮ ለቀጣይ 20 ቀናት የሚሰጥ ሲሆን 1,749 ሰልጣኞች እንደሚሳተፉ ለማወቅ ተችሏል።
