የግብርና ቆጠራ አፈፃፀምና የመካከለኛ ዘመን እቅድ ላይ ውይይት ተደረገ

ህዳር 27/2017ዓ.ም፣ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት በመካከለኛ ዘመን ከ2016-2018ዓ.ም አቅዶ እያከናወናቸው ከሚገኙቱ ጥናቶችና ቆጠራ አንዱ በሆነው ሁለተኛ ዙር የግብርና ቆጠራ ያለበት አፈፃፀም ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አደረገ።

በውይይት መድረኩ የተገኙት የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ፍፁም አሰፋ በመካከለኛ ዘመን ታቅደው እየተከናወኑ ካሉት ጥናቶችና ቆጠራ የሚገኙ መረጃዎች በቀጣይ ለሚዘጋጁ እቅዶችና ፖሊሲዎች ግብዓት የሚሆኑ መረጃዎች መሆናቸውን በመግለጽ ለዋጋ ግሽበት፣ የሀገር ውስጥ ምርት እድገትን ለማስላት መነሻ ወሳኝ የሆኑ መረጃዎች የሚገኝበት መሆኑን ገልፀዋል።  ከቆጠራው በሚገኙ መረጃዎች መሻሻል ያለባቸው የጥናት ስነ-ዘዴዎችን ለማሻሻል የሚያግዙ ግብዓቶች እንደሚገኙበት ተናግረዋል።  የክልል የግብርና ቢሮ ሀላፊዎች፣ የክልል ፕላንና ልማት ቢሮ ሀላፊዎች ለዚህ ቆጠራ ስኬት እስከቀበሌ ድረስ በሚኖራቸው ግንኙነት ሀላፊነት በመውሰድ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመድረኩ የስነ-ህዝብና ጤና ጥናት፣ ብሔራዊ የተቀናጀ የቤተሰብ ጥናትን በሚመለከት የጥናቶቹ ስነ-ዘዴ ላይ እንዲሁም የግብርና ቆጠራ ከመጀመሪያ ጀምሮ አሁን ያለበትን አፈፃፀም የሚያሳዩ ገለፃዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የግብርና ቆጠራ መረጃ ዓላማውን፣ ከመረጃውን የሚገኘው ጠቀሜታ ላይ ግንዛቤ በመፍጠር፣ ለሚያጋጥሙ ችግሮች ፈጣን ምላሾችን በመስጠት፣ ለስራው ክትትል በማድረግ ድጋፍ እንዲያደርጉ በመድረኩ ለተገኙት አመራሮች የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ግርማ አመንቴ በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ ከግብርና ሚኒስቴር፣ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከክልል ፕላንና ልማት ቢሮ፣ ከክልል ግብርና ቢሮ የተውጣጡ አመራሮችና ከፍተኛ ባለሙያዎች በውይይት መድረኩ ተሳትፈዋል።