ሐምሌ 9/2017ዓ.ም አዳማ ፣

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አግልግሎት በ2018ዓ.ም ለሚያካሄደው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ የቅድመ አሰልጣኞች ስልጠና ከዋና መሠሪያ ቤትና 26ቱ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ለተወጣጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች እየተሰጠ ይገኛል።

የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ክቡር ዶ/ር በከር ሻሌ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት በ2018ዓ.ም የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት እያከናወነ መሆኑን አንስተው ከነዚህ የቅድመ ዝግጅት ተግባር መካከል አንዱ በየደረጃው በቆጠራው ስራ የሚሳተፈውን የሰው ሀይል በጥራት አሰልጥኖ ለስራው ዝግጁ ማድረግ ሲሆን ዛሬ በሚጀመረው ስልጠና የሚሳተፉ ሰልጣኞች በቀጣይ በቆጠራው መስክ ስራ የሚሳተፈውን የሰው ሀይል የመሰልጠን ትልቅ ሀላፍነት ያለበቸው መሆኑን በመገንዘብ ስልጠናውን በከፍተኛ ትኩረትና ስነ-ምግባር መከታተል እንደሚጠበቅባቸው መመሪያ በመስጠት ስልጠናውን አስጀምረዋል።


ስልጠናው ከሐምሌ 9 ጀምሮ ለቀጣይ 20 ቀናት በቆጠራው ስነ ዘዴ፣ ፅንሰ ሀሳብ፣ የቆጠራው መጠይቆች፣ መረጃውን ለመሰብሰብ የሚውሉ ሶፍትዌርና የታብሌት ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ የተሟላ ዕውቀትና ግንዛቤ ለመፍጠር በሚያስችል ደረጃ በተቋሙ የቢዝነስ ስታቲስቲክስ ከፍተኛ ባለሙያዎች እንደሚሰጥ ከስልጠናው መርሀ ግብር ለማወቅ ተችሏል። በስልጠናው ከዋናው መስሪያ ቤትና ከቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የተውጣጡ በቁጥር 236 የሚሆኑ ባለሙያዎች ይሳተፉበታል።

