ጥር 7/2017ዓ.ም፣ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት በፍልሰት መረጃ አያያዝና ቅብብሎሽ ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ከፍትህ፣ ውጪ ጉዳይ፣ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከፖሊስ ኮሚሽንና ከሌሎች ስምንት ተቋማት ጋር ተፈራረመ።
በስምምነት መድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር በከር ሻሌ ተቋማቸው የሀገሪቱን የመረጃ ፍላጎት ለማሟላት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልፀው፤ ዛሬ ከተቋማቱ ጋር የሚደረገው የመግባቢያ ስምምነትም የዚህ አካል እንደሆነ በማስረዳት በሀገራችን የተሟላ የፍልሰት መረጃ አቅርቦት እንዲኖር ከተቋማቱ ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ገልፀዋል።
በመድረኩ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፍትህ ሚኒስትር ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ በየተቋማቱ የሚገኙ የፍልሰት መረጃዎችን ወደአንድ በማሰባሰብ ከአንድ ቋት ለመጠቀም እንዲቻል በመመሪያ ቁጥር 563/13 ሀላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ ስታቲስክስ አገልግሎት የሚተገበረውን የፍልሰት የመረጃ አስተዳደር ቡድን እና መረጃ ምንጮች መካከል ስራውን ለማስጀመር የተደረገ ስምምነት መሆኑን አንስተው ሁሉም ተቋማት በስምምነቱ ላይ የተመለከተውን ሀላፊነትን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በስምምነቱ በየተቋማቱ የሚገኘውን የፍልሰት አስተዳደራዊ መረጃዎችን ለኦፊሺያል ስታቲስቲክስ መጠቀም በሚያስችል ጥራትና ደረጃ በማደራጀት ለስታቲስቲክስካዊ መረጃ አገልግሎት እንዲውሉ የሚያስችል ተግባራቶች የሚከናወኑ ሲሆን እነዚህን ተግባራት ለማሳለጥ የሚያስችል የፍልሰት የመረጃ ቋትና መረጃን ለማልማት የሚውሉ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ይደራጃል።