ዓመታዊ የስታቲስቲክስ መጽሔት ለተጠቃሚዎች ይፋ ተደረገ

ጥር 27/2017ዓ.ም፤ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የ2015 ዓ.ም ዓመታዊ የስታቲስቲክስ መጽሔት /Statistical Abstract/ የህትመት ስርጭት ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ለተጠቃሚዎች ይፋ ተደረገ።

በመድረኩ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር በከር ሻሌ ለተቋሙ የመረጃ ምንጭ አንዱ ከአስተዳደራዊ መዛግብት የሚገኙ መረጃዎች መሆናቸውን ገልጸው የአስተዳደራዊ መዛግብት መረጃ ከተለያዩ ተቋማት በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በስነ-ህዝብ እና ሌሎች ኦፊሻላዊ መረጃዎችን በመሰብሰብ ስታንዳርዱንና ስታቲስቲካዊ ይዘቱን በመጠበቅ መረጃውን በማጠናቀር እና በቴክኖሎጂ ተደግፎ ተጠቃሚዎች መረጃን ከአንድ ማዕከል እንዲያገኙ ለማድረግ የሚያስችል ነው ሲሉ ገልፀዋል። መረጃው ላለፉት ዓመታት በዲጂታል ፕላትፎርም ብቻ ሲሰጥ የቆየ ሲሆን የተጠቃሚዎችን ፍላጎትን ከግምት ውስጥ በማስገባት አሁን ላይ በህትመት መልክ ተዘጋጅቶ ለተጠቃሚዎች ዝግጁ መሆኑን አክለው ገልፀዋል።

በመድረኩ የስታቲስቲክስ መፅሔቱ አጠቃላይ ይዘት፣ መረጃው የተሰበሰበባቸው ተቋማት፣ የተሰበሰቡ መረጃዎች፣ መረጃውን በመሰብሰብ ሂደት ወቅት ያጋጠሙ ችግሮችን፣ በቀጣይ መደረግ ስላለባቸው መፍትሄ ሀሳቦች ላይ በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የአስተዳደር እና የማህበራዊ ስታቲስቲክስ ዴስክ ሀላፊዎች ገለፃ የሰጡ ሲሆን፣ የስታቲስቲክስ መጽሔት /Statistical Abstract/ መረጃውን በግራፍ፣ በሰንጠረዥ፣ በካርታና መረጃ ተጠቃሚዎች በሚፈልጉት ፎርማት አመላካቾችን በማስገባት መረጃውን በዲጂታል ፎርም ማግኘት እንደሚቻል የሚያሳይ /Integrated management information system/IMIS/ ላይ ከ UNFPA በመጡ ባለሙያ ገለፃ ቀርቦ ውይይት የተደረገ ሲሆን ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።

በመጨረሻም የ2015ዓ.ም ዓመታዊ የስታቲስቲክስ መፅሔት /Statistical Abstract/ በተቋሙ ድረ ገጽና በህትመት ተዘጋጅቶ ለተጠቃሚዎች ይፋ መሆኑ በተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ተገልጿል።