የኢትዮጵያ ሥነ-ህዝብና ጤና ጥናት ከመስክ መረጃ የመሰብሰብ ተግባር ተጠናቀቀ

ግንቦት 5/2017ዓ.ም አዲስ አበባ፣

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የ2024 ኢትዮጵያ ሥነ-ህዝብ ጤና ጥናት ከመስክ መረጃ የመሰብሰብ ተግባር ማጠናቀቁን ለሀገር አቀፍ አብይ ኮሚቴና አለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች ገለፀ።

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ፍፁም አሰፋ መድረኩ የተዘጋጀው አምስተኛ ዙር የኢትዮጵያ ሥነ-ህዝብ ጤና ጥናት ከመስክ መረጃ የመሰብሰብ ተግባር መጠናቀቁንና ጥናቱ አሁን ላይ የደረሰበትን ደረጃ ለማሳወቅ የተዘጋጀ መሆኑን በመግለጽ መድረኩን አስጀምረዋል።

የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር መቅደስ ዳባ ከጥናቱ የሚገኙ መረጃዎች በጤናው ዘርፍ በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ እቅዶችና ፖሊሲዎችን ለማዘጋጀት የረጅም ጊዜ እይታ እንዲኖር እንደሚያደርግ ገልፀው ስራው ቀጣይነት ያለውና የተሳካ እንዲሆን ከኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

አምስተኛ ዙር የኢትዮጵያ ሥነ-ህዝብ ጤና ጥናት የቅድመ ዝግጅት ተግባራት፣ ለጥናቱ የተመረጡ ናሙናዎች፣ የጥናቱን ስነ-ዘዴ፣ ያጋጠሙ ችግሮችና የተወሰዱ መፍትሄዎችና ጥናቱ አሁን ላይ የደረሰበትን ደረጃ የሚያሳይ ገለፃ በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የስነ-ሕዝብ ስታቲስቲክስ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ሀይለማርያም ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽ ተሰጥቶበታል።

በተጨማሪም የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ፍፁም አሰፋ በዚህ ጥናት ለተሳተፉና ድጋፍ ላደረጉ መንግስታዊና አለም አቀፍ ድርጅቶች ምስጋናቸውን አቅርበው በቀጣይ ቀሪ ስራዎች ላይ አቅጣጫ በመስጠት መድረኩ ተጠናቋል።

aa3a9519
aa3a9491
aa3a9481
aa3a9494