ግንቦት 19/2017ዓ.ም አዲስ አበባ፣
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት በ2017ዓ.ም እያካሄደ በሚገኘው የግብርና ቆጠራ አፈፃፀምና በቀጣይ ቀሪ የቆጠራው ተግባራት ላይ ከአለም አቀፍ የምግብና ግብርና ድርጅት (FAO) ጋር ውይይት አደረገ።
የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ክቡር ዶ/ር በከር ሻሌ ተቋሙ ለሁለተኛ ጊዜ እያካሄደ የሚገኘውን የግብርና ቆጠራ ከፍተኛ በሆነ በመንግስትና አጋር ድርጅቶች ድጋፍ አሁን ያለበት ውጤታማ የሆነ አፈፃፀም ላይ መድረሱን ገልፀው አለም አቀፍ የምግብና ግብርና ድርጅት (FAO) እያደረገ ላለው የቴክኒክ ድጋፍ በተቋሙ ስም አመስግነዋል። ተቋሙ በቀጣይ ቀሪ የቆጠራው ተግባራት ከድርጅቱ የቴክኖሎጂና የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚፈልግም ዋና ዳይሬክተሩ አክለው ገልፀዋል።

የአለም አቀፍ የምግብና ግብርና ድርጅት (FAO) የግብርና ቆጠራ ቡድን መሪ ሄሮ ካስታኖ (Ph.D) የግብርና ቆጠራው ጥሩ አፈፃፀም ላይ እንደሆነ እና በቀጣይ ቀሪ ስራዎች ላይ ከተቋሙ ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

የግብርና ቆጠራ ከቅድመ ዝግጅት አሁን እስካለበት ደረጃ ያለውን አፈፃፀም እንዲሁም ቀሪ ተግባራትን የሚያሳይ ገለፃ በግብርና ስታቲስቲክስ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ አብዱላዚዝ ሽፋ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በኢኮኖሚ ስታቲስቲክስ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን ቀሬና በተቋሙ ከፍተኛ ባለሙያዎች ምላሽ ተሰቶበታል።