
መስከረም 5/2018ዓ.ም አዲስ አበባ፣
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት በ2018 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚያካሂደው የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ስራ የሚሰማሩ መረጃ ሰብሳቢዎች፣ ተቆጣጣሪዎችና ስታቲሺያኖች በአዲስ አበባና በሁሉም ክልሎች በተዘጋጁ ከ53 በላይ የስልጠና ማዕከላት መስጠት ተጀመረ።

የስልጠናው ዓላማ ለሀገራችን የኢኮኖሚ ዘርፍ የጎላ ፋይዳ ያላቸውን ስታቲስቲክስ መረጃዎች በጥራት በመሰብሰብ ለሚፈለገው ዓላማ ማዋል የሚያስችል የሰው ሀይል ለማዘጋጀት ታስቦ የሚሰጥ እንደሆነ በአዲስ አበባ ከተማ በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ የስልጠና ማዕከል የተገኙት የቢዝነስ ስታቲስቲክስ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ናቃቸው ነጋሽ ገልፀዋል። ስልጠናውን በተሟላ መልኩ ለመስጠት የሚያስችል ሁሉን አቀፍ ዕቅድ ታቅዶና በቂ ዝግጅት ተደርጎ የተጀመረ በመሆኑ ሰልጣኞች በመስክ ለሚጠበቅባቸው ስራ ራሳቸውን ለማብቃት ለስልጠናው ሙሉ ትኩረት መስጠት እንደሚገባቸውና አሰልጣኞች ለስራ የሚፈለገውን ብቁ የሰው ሀይል የማፍራት ታላቅ ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው እንዲሁም የአከባቢው መስተዳደር አካላት ስልጠናው በታቀደው መሰረት ተሰጥቶ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባቸው የሚገልፅ መልዕክት በሁሉም የስልጠና ማዕከላት የተላለፈ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል።

ስልጠናው በ54ቱ ማዕከላት ከዛሬ ጀምሮ ለሚቀጥሉት 25 ቀናት ስለቆጠራው ፅንሰ ሀሳብ፣ የተግባርና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ በማተኮር እንደሚሰጥ ከወጣው መርሀ ግብር ለመረዳት ተችሏል።

በስልጠናው በቆጠራው ከመስክ መረጃ የሚሰበስቡ መረጃ ሰብሳቢዎችና ተቆጣጣሪዎች በአጠቃላይ ከ39ሺ ሰዎች በላይ ይሳተፉበታል።

