
መስከረም 26/2018ዓ.ም አዲስ አበባ፣
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት በ2017ዓ.ም ባካሄደው የግብርና ቆጠራ የተገኙትን ልምዶች ለናሚቢያ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የማካፈል የስልጠና መርሀ-ግብር በተቋሙ ዋና መስሪያ ቤት እየሰጠ ይገኛል።

በመድረኩ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ክቡር ዶ/ር በከር ሻሌ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የግብርና ዘርፍ ስታቲስቲክስ መረጃዎች ከአመታዊ የግብርና ናሙና ጥናት በመሰብሰብ፣ በማጠናቀርና ሪፖርት አዘጋጅቶ ለመንግስትና ለሌሎች የዘርፋ መረጃ ተጠቃሚዎች ተደራሽ በማድረግ የብዙ አመታት ልምድ ያካበተና በአፍሪካ አህጉርም ቀዳሚ ተቋም መሆኑን አንስተው ተቋማቸው ከዚህ ቀደም ለዘመናት በስራ ውስጥ ያካበተውንና በ2017ዓ.ም ለሁለተኛ ጊዜ ባካሄዳው የግብርና ቆጠራ የተገኙትን ልምዶችና ተሞክሮዎች ለናሚቢያ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ለማካፈል ዕድሉ በማግኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው የዚህ አይነቱ በአፍሪካ ሀገራት አቻ ተቋማት መካካል የሚደረገው የልምድ ልውውጥ በአህጉረ አፍሪካ ጠንካራ የስታቲስቲክስ ተቋማት ግንባታ ስትራቴጅ አካል በመሆኑ በቀጣይም ተጠነክሮ መቀጠል እንደሚገባው መልዕክታቸውን በማስተላለፍ መርሀ-ግብሩን አስጀምረዋል።

የስታቲስቲክስ ዲጂታላይዜሽን ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሜሮን ክፈለው እንዳሉት የመድረኩ ዓላማ ተቋማችን በስታቲስቲክስ ልማት ፕሮግራም (ከ2016 -2018ዓ.ም)በመካከለኛ ዘመን እቅድ ካከናወናቸው ተግባራት አንዱ በ2017 ዓ.ም የተካሄደው የግብርና ቆጠራ ከመስክ መረጃ የመሰብሰብ ተግባር አጠናቀን መረጃ የማጥራት የሪፖርት ዝግጅት ስራ ላይ እንገኛለን ያሉ ሲሆን ከግብርና ቆጠራ ያገኘናቸውን ስኬቶችና ያጋጠሙን ችግሮች የተወጣንበትን መንገድ ልምድ ለማካፈል ሲሆን ናሚቢያ ስታቲስቲክስም ያሉትን ልምዶች ለመጋራት ዝግጁ ነን ሲሉ ገልፀዋል።

በመድረኩ የናሚቢያ የኢኮኖሚ ስታቲስቲክስ ዘርፍ ኃላፊና የልኡክ ቡድኑ መሪ ዶ/ር ማቡኩ ሙቡሲሲ ስለናሚቢያ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ አጠቃላይ ገለፃ ቀርቦ አቅርቦው ስለተቋማቸው ግንዛቤ አስጨብጠዋል።

የልምድ ልውውጥ መርሀ ግብሩ ለሚቀጥሉት አምስት ቀናት እንደሚቀጥል ከወጣው መርሀ ግብር ለመረዳት ተችሏል።

