
ህዳር 10/2018 ዓ.ም አዲስ አበባ፣
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ከስታቲስቲክስ ኖርዌይ ጋር በመተባበር የአስተዳደራዊ መረጃዎችን ለኦፊሺያል ስታቲስቲክስ መጠቀም የሚያስችል ስልጠና ከፌዴራል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ለተውጣጡ ባለሙያዎች ተሰጠ።

በስልጠናው መድረክ ተገኝቷ መልዕክት ያስተላለፋ የስታቲስቲክስ ኖርዌይ አቅም ግንባታ ፕሮጀክት አማካሪ ሚስተር ሳዲቅ ኪዌሲ ስታቲስቲክስ ኖርዌይ ከኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ጋር በተለያዩ የስታቲስቲክስ አቅም ግንባታ ተግባራት ላይ በትብብር እየሰራ መሆኑን አንስተው የዛሬው ስልጠናም አስተዳደራዊ መረጃዎች ለኦፊሺያል ስታቲስቲክስ መረጃ ምንጭነት መጠቀም በሚያስችል ስነዘዴ ላይ በአስተዳደራዊ መረጃ ላይ ለሚሰሩ የሴክተር መስሪያ ቤት ባለሙያዎች ግንዛቤ ለመፍጠር የተዘጋጀ መሆኑን ገልፀዋል። በስልጠናው አስተዳደራዊ መረጃዎች አጠቃቀም፣አደረጃጀት፣ከአስተዳደራዊ መረጃዎች ጥራት ያለው ኦፊሺያል ስታቲስቲክስ መረጃዎች ማመንጨት በሚያስችል ስነዘዴ ላይና ሌሎች ርዕሶች ላይ በዘርፋ የካበተ ልምድና ዕውቀት ባለቸው የስታቲስቲክስ ኖርዌይና የተቋሙ ባለሙያዎች ገለፃ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በስልጠናው ከገቢዎች ሚኒስቴር፣ ከንግድ ሚኒስቴር፣ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ከሲቪል ምዝገባና ነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲና ሌሎች ተቋማት የተውጣጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
