ህዳር 15/2018ዓ.ም አዳማ፣

የሲቪል ሰርቪስ ከኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ጋር በመተባበር በመላ ሀገሪቱ የሚገኙትን የመንግስት ሰራተኞች ቁጥር መረጃ የማረጋገጥ የሙከራ ተግባራት ላይ ለሚሰተፉ መረጃ ሰብሳቢዎች ስልጠና በአዳማ መስጠት ተጀመረ።

በስልጠናው ማስጀመሪያ መድረክ ላይ የተገኙት የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ክቡር አቶ ሽብሩ አባዲማ ተቋማቸው ቀልጣፋና ውጤታማ ህዝብ አገልጋይ የሲቪል ሰርቪስ ለመፍጠር ሪፎርም በማካሄድ በአሁኑ ጊዜ ወደ ተሟላ ትግበራ ለመግባት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ገልፀው የሪፎርሙን ቀጣይነት ለማረጋገጥ በመንግስት ተቋማት ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች ቁጥር ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ የተረጋገጠ መረጃ መያዝ አስፈላጊ በመሆኑ በሀገራችን የሚገኙትን ሰራተኞች መረጃ ለመረጋገጥ በዘርፉ የካበተ ልምድና እውቀት ካለው የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ጋር ለመስራት የሚያስችል ቅድመ ሁኔታ ተጠናቆ ዛሬ ለስራው የሚያስፈልገውን የቅድመ ዝግጅት ተግባር በመስክ መረጃ ሰብሳቢዎች ስልጠና ማስጀመራቸውን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ክቡር ዶ/ር በከር ሻሌ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ በሀገራችን በመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጥረው የሚሰሩትን ሰራተኞች ቁጥር መረጃ የማረጋገጥ ስራ ከተቋማቸው ጋር ለመስራት በመወሰኑ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው፤ ተቋማቸው በዘርፉ ያለውን ልምድ፣ ዕውቀት፣ ቴክኖሎጂና መሰረተ ልማት በማስተባበር ይህን ለሀገርና ለኮሚሽኑ ከፍተኛ ትርጉም ያለው ተግባር በጊዜና በጥራት ሰርቶ ለማስረከብ በትጋት እንደሚሰራ ገልፀዋል።

ለስራው ከተለያዩ የሀገርቱ ዩኒቨርሲቲ ለተወጣጡ መምህራኖች ለሚቀጥሉት አምስት ቀናት የሰራተኞች ቁጥር መረጃ ለማረጋገጥ በተዘጋጁ ስነ-ዘዴዎችና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዩች ላይ የጽንሰ ሀሳብና የተግባር ስልጠና እንደሚሰጥ ከስልጠናው መርሀ-ግብር ለመረዳት ተችሏል።

