
መጋቢት 14/2018 ዓ.ም አዳማ፣
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት በየወሩ በሚያወጣው የዋጋ ስታቲስቲክስ ጥናት መረጃ ላይ ከ26ቱ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ለተውጣጡ የዋጋ ስታቲስቲክስ መረጃ ሰብሳቢዎች፣ ተቆጣጣሪዎችና ስታቲስቲሺያኖች ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።

የስልጠናውን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ክቡር ዶ/ር በከር ሻሌ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት በ2017 ዓ.ም ትላልቅ ቆጠራና ጥናቶችን ማካሄዱን አንስተው የዋጋ ጥናት መረጃ በየወሩ የሚሰራ፣ የማይቋረጥ አስፈላጊና ወሳኝ የማክሮ ኢኮኖሚ ግብዓት በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው መረጃ መሆኑን ገልፀው፤ በዚህ ጥናት የመስክ ስራ ላይ የተሰማራችሁ መረጃ ሰብሳቢዎች፣ ስታቲስቲሺያኖችና ተቆጣጣሪዎች ስልጠናውን በመከታተል ጥራት ያለው የዋጋ ስታቲስቲክስ መረጃ መሰብሰብ አለባችሁ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የዋጋ ስታቲስቲክስ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ አለማየሁ ተፈሪ ይህ ስልጠና የተዘጋጀበት ዋና ዓላማ በመስክ ስራ ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን በመለየትና በመፍታት ለመረጃ ጥራት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ገልፀው፤ በዋጋ ስታቲስቲክስ ጥናት ፅንሰ ሃሳብ፣ ስለጥናቱ አስፈላጊነትና የመረጃ ጥራት ላይ ያተኮረ ገለፃ ቀርቦ ግንዛቤ ተፈጥሯል።

ስልጠናው ከ26ቱ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ለተውጣጡ በመስክ ስራ ላይ ለሚሳተፉ 300 የሚሆኑ ባለሙያዎች ለቀጣይ ሰባት ቀናት እንደሚሰጥ ከወጣው መርሀ ግብር ለመረዳት ተችሏል።


