
ህዳር 29/2018 ዓ.ም አዲስ አበባ፣
የመካከለኛ ዘመን (ከ2016-2018 ዓ.ም) የስታቲስቲክስ ልማት ስትራቴጂ ዕቅድ አፈፃፀም ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር የማክሮ ኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ ክቡር አምባሳደር ግርማ ብሩ እና የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ፍፁም አሰፋ በተገኙበት ውይይት ተደረገ።

የመካከለኛ ዘመን ዕቅዱን ለማሳካት የታቀዱ የስታቲስቲክስ ልማት ስትራቴጂክ ዕቅድ የእስከአሁን አፈፃፀም ያለበት ደረጃ በተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ክቡር ዶ/ር በክር ሻሌ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን በዕቅድ ዘመኑ ሊከናወኑ ከታቀዱት ተግባራት መካከል አምስተኛ ዙር የስነ-ህዝብና ጤና ጥናት የመጀመሪያ ሪፖርት ዝግጅት መጠናቀቁ፣ የግብርና ቆጠራና ብሔራዊ የተቀናጀ የቤተሰብ ጥናት የመስክ ስራ ተጠናቆ የሪፖርት ዝግጅት ላይ እንደሚገኝ እንዲሁም በዕቅድ ዘመኑ እንዲከናወን የሚጠበቀው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ በዚህ ዓመት ከጥቅምት ጀምሮ እየተካሄደ መሆኑ ተገልጿል።

በሌላ መልኩ ተቋሙ በቀጣይ የሀገሪቱን የስታቲስቲክስ መረጃ አቅርቦት ፍላጎትን በተሻለ ጥረትና ወቅታዊነት ለማሟላት የሚያስችለውን ተቋማዊ ቁመና ለመገንባት ሁሉን አቀፍ ሪፎርም እያከናወነ መሆኑ ተገልጿል።

ስታቲስቲክስ የሀገር ሉዓላዊነት መገለጫ መሳሪያ መሆኑን የገለፁት የጠቅላይ ሚኒስቴር የማክሮ ኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ ክቡር አምባሳደር ግርማ ብሩ ስታቲስቲክስን ለማስተዳደር፣ ለማስተዋወቅና ጥቅም ላይ እንዲውል መሰራት እንዳለበት ጠቅሰው ተቋሙን ለቀጣይ ተልዕኮ ዝግጁ ለማድረግ እየተሰሩ ባሉት ተግባራት ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ፍፁም አሰፋ ተቋሙ የሀገሪቱ የስታቲስቲክስ መረጃ አቅርቦት ማዕከል ሆኖ እንዲወጣ የሚያስችል የስታቲስቲክስ አዋጅ ማሻሻያ ማድረግና የተሟላ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲኖረው ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው በትኩረት እየሰራ መሆኑ ገልፀው በመካከለኛ ዘመን የስታቲስቲክስ ልማት ስትራቴጂ ዕቅድ አፈፃፀም ውጤታማ እንደነበር በማስረዳት ቀሪ ስራዎችን ለማጠናቀቅ በተጀመረው ትኩረት መስራት እንደሚገባ የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።
በተጨማሪም በተቋሙ ዋና መስሪያ ቤት የተሰሩ የሪፎርም ስራዎችን ጎብኝተዋል።


