
ሚያዚያ 7/2018 ዓ.ም አዲስ አበባ፣
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር በጋራ ለሚካሂደው የመንግስት ሰራተኞች መረጃ ለማረጋገጥ ለሚሰማሩ መረጃ ሰብሳቢዎችና ተቆጣጣሪዎች በሀገሪቱ በተዘጋጁ 9 የስልጠና ማዕከላት መሰጠት ተጀመረ።


ስልጠናውን ከማዕከል በበይነ መረብ ያስጀመሩት የተቋሙ ዋና ዳ/ር ክቡር ዶ/ር በከር ሻሌ ሀገራችን ኢትዮጵያ ያለመችውን ብልፅግና እውን ለማድረግ ከነደፈቻቸው ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች አንዱ የልማት አቅም የሆነውን የሀገሪቷ የሲቪል ሰርቪስ ተቋምና አስፈፃሚዎችን ማዘመን፣ ብቃትና ስነ ምግባር ማነፅ እንዲሁም የማስፈፀም አቅም ማሳደግ አንዱ የሪፎርም አካል ነው ያሉ ሲሆን የተረጋገጠና ጥራት ያለው የሲቪል ሰርቪስ መረጃ መኖሩ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል። ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም በዚህ ስልጠና የምትሳተፉ መረጃ ሰብሳቢዎችና ተቆጣጣሪዎች ተልዕኮውን በሚገባ በመረዳትና ስልጠናውን በአግባቡ በመከታተል፣ በቂ ዕውቀትና ክህሎት በመጨበጥና በቡድን በመስራት ስራው የተሳካ እንዲሆን ሀገራዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።


በበይነ መረብ ንግግር ያደረጉት የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር መኩሪያ ኃይሌ ተቋማቸው ይህን ስራ ለማሳካት ከኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ጋር በቂ ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን አንስተው፤ ስራው ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆንና በሀገሪቷ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ግንባታ ላይ ያለውን ፋይዳ በመረዳት ጥራት ያለው የሰው ኃይል መረጃ በትምህርት ደረጃ፣ የሰው ኃይል ብዛት ለማወቅ፣ በየተቋማቱ ያሉትን ክፍት የስራ መደቦች ለመለየትና የተሟላ መረጃ ለማግኘት መሆኑን አንስተው ከዚህ ስራ የሚገኘው መረጃ መንግስት በመረጃና በማስረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ እንዲሰጥ ያግዛል ሲሉ ገልፀዋል። በተጨማሪም ኮሚሽነሩ ለዚህ ስራ መሳካት ድጋፍ ላደረጉ የክልል ቢሮ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶችና አመራሮች፣ በዚህ ስራ ለሚሳተፉ ባለሙያዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በስልጠናው ከሀገሪቷ ዩኒቨርስቲዎችና ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት የተውጣጡ መምህራንና ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት በመረጃ መሰብሰብ ላይ ሲሰሩ የነበሩ ከ 4,000 በላይ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

