ግንቦት 12/2018 ዓ.ም አዲስ አበባ፣
በፕላንና ልማት ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ሀገራዊ ጉባኤ መጠናቀቁ ተገለፀ።
በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በረከት ፍስሀፅዮንና የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ክቡር ዶ/ር በከር ሻሌ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።

ለሶስት ቀናት የተዘጋጀው ሀገራዊ ጉባኤ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ አንፃር የተሰሩ ስራዎችና መረጃዎችን ለውሳኔና ፖሊሲ ለማውጣት ከመጠቀም አንፃር በርካታ እመርታዎች የታየበት መድረክ መሆኑን የገለፁት የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በረከት ፍስሀፅዮን በጉባኤው ከስታቲስቲክስ ሉዓላዊነት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች፣ ከቴክኖሎጂ አንፃር የተሰሩና በቀጣይ የሚሰሩ ስራዎች፣ ዜጎች በስታቲስቲክስ ስርዓት ስላላቸው ሚና፣ ሀገራችን በቀጣይ ለምታደርገው የሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት ክለሳ (GDP Rebasing) ከተለያዩ ተቋማት ከተውጣጡ ኃላፊዎች ጋር ውይይት የተደረገበትና ግንዛቤ የተፈጠረበት ጉባኤ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ክቡር ዶ/ር በከር ሻሌ ተቋማቸው ባለፋት ሶስት ቀናት ያስተዋወቃቸው ዋና ዋና ጉዳዮች በስታቲስቲክስ ልማት ፕሮግራም በመካከለኛ ዘመን እቅድ (ከ2016-2018 ዓ.ም) ያከናወናቸው የስነ-ሕዝብና ጤና ጥናት፣ የተቀናጀ የቤተሰብ ጥናት፣ የግብርና ቆጠራና የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ አፈፃፀም፣ ጥናቶችና ቆጠራዎቹን ለማከናወን የተጠቀማቸው ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችና መሳሪያዎች፣ የመረጃ ጥራትና ተዓማኒነት ላይ ትኩረት ማድረጉን ገልፀዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ይህ ሀገራዊ ጉባኤ ስለስታቲስቲክስ ስራዎች ግንዛቤ የተፈጠረበትና ተቋሙ ለሚያደርገው የልህቀት ጉዞ መመሪያ የተላለፈበት መድረክ መሆኑን ገልፀዋል።

በአጠቃላይ በጉባኤውና በኤግዚቢሽኑ ላይ ከ40 የመንግስትና የግል ተቋማትና የሲቪል ማህበራት የተውጣጡ ኃላፊዎችና ከ30 ሺ በላይ ዜጎች ተሳትፈዋል።
