መጋቢት 24/2018 ዓ.ም ፣

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የስራ ፈጠራ፣ የደንበኞች አገልግሎትና የጊዜ አጠቃቀም ለማሳደግ የሚያስችል ስልጠና ድጋፍ ለሚሰጡ ሰራተኞች እየሰጠ ይገኛል።


በመድረኩ ተገኝተው ስልጠናውን ያስጀመሩት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብነት ሐዋዝ ተቋሙ ባለፋት ሶስት ዓመታት ተግባራዊ እያደረገ በሚገኘው ተቋማዊ ሪፎርም አንዱና ዋነኛው ትኩረት የሰው ሀይልን የመፈፀም ብቃትና ክህሎት ቀጣይነት ባለው መልኩ ማሻሻል እንደሆነ አንስተው የዛሬው ስልጠናም የስራ ፈጠራ፣ የጊዜ አጠቃቀም፣ የደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥ፣ አዳዲስ አሰራሮችና መፍትሄዎች ማምጣት ላይ ትኩረቱን አድርጎ የተዘጋጀ መሆኑን ገልፀዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ አዚዛ እስማኤል በተቋሙ በምታከናውኗቸው የዕለት ተዕለት ተግባራት የተቋማችንን ግቦች ለማሳካትና የስራ ፈጠራን በማሳደግ በግል ህይወታችሁም ላይ ለውጥ እንድታመጡ ታስቦ የተዘጋጀ ስልጠና በመሆኑ ስልጠናውን በአግባቡ በመከታተል ተግባር ላይ እንድታውሉ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ስልጠናው ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ በመጡት ዶ/ር አወቀ አሸናፊ በስራ ፈጠራ፣ የደንበኞች አገልግሎትና አያያዝ እንዲሁም የጊዜ አጠቃቀምና ሌሎች ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ለቀጣይ አምስት ቀናት እንደሚሰጥ ከወጣው መርሀ ግብር ለመረዳት ተችሏል።