ግንቦት 10/2018 ዓ.ም አዲስ አበባ፣

‘’የመረጃ ሉዓላዊነት ለፖሊሲ ነፃነት ‘’ በሚል በፕላንና ልማት ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት በጋራ የተዘጋጀ ሀገራዊ ጉባኤ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ክቡር ዶ/ር ዐብይ አህመድን ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት እየተካሄደ ይገኛል።

መረጃ ሀገራዊ ራዕያችን የሆነውን ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት፣ የፖሊሲ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ዋነኛ ግብዓት መሆኑን አንስተው ይህን መረጃ በሀገር ባለሙያዎች ዕውቀትና ክህሎት በመሰብሰብ፣ በመተንተን በመረጃ ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ ለማውጣትና ዕቅዶችን ለማቀድ ወሳኝ ግብዓት መሆኑን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ክቡር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ገልፀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም የምናመነጫቸው የስታቲስቲክስ መረጃዎች መሬት ላይ ወርደው የማህበረሰቡ ህይወት ላይ ተጨባጭ የሆነ ለውጥ ማምጣት አለባቸው ሲሉ ገልፀዋል።

የዕለቱን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ፍፁም አሰፋ በሪፎርም ለውጡ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ የስታቲስቲክስ መረጃ መሆኑን አንስተው ባለፉት ሶስት ዓመታት የስታቲስቲክስ ስትራቴጂክ ልማት ፕሮግራም በመቅረፅ ወሳኝ የሆኑ ጥናቶችና ቆጠራዎችን በማካሄድ ትላላቅ ስኬቶችና እመርታዎች መመዝገባቸውን ገልፀው፤ የሚገኙት መረጃዎችም ፖሊሲዎችን ለማውጣት፣ እቅድ ለማዘጋጀትና በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ለመስጠትን ዲጂታል ኢኮኖሚን እውን ለማድረግ ወሳኝ ነው ሲሉ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ባለፉት ሶስት ዓመታት ባከናወናቸው ጥናቶችና ቆጠራዎች መረጃዎችን ለመሰበሰብ ሙሉ ለሙሉ የታብሌት ቴክኖሎጂ የተጠቀመ ሲሆን በተጨማሪም ዘመናዊ የጂ አይ ኤስ (GIS) ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የቆጠራ ቦታዎችን የማካለል ስራ፣ መረጃ ሰብሳቢዎች በተመደቡበት ቆጠራ ቦታ ላይ መገኘታቸውን በትራኪንግ ዘዴ ( tracking system) በመቆጣጠር፣ የሳተላይት ምልከታን ተጠቅሞ የግብርና ቆጠራን መረጃ በመሰብሰብ ጥራትና ወቅታዊነታቸውን የጠበቁ መረጃዎችን ለተጠቃሚዎች ለማቅረብ እየሰራ መሆኑ ተገልጿል።


በጉባኤው ላይ በተዘጋጀው ኤግዚቢሽን ላይ በፕላንና ልማት ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የመረጃ መሰብሰብና ስርጭት ፕላትፎርሞች፣ የጂ አይ ኤስ (GIS) ቴክኖሎጂ፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች ተጎብኝተዋል።



