ግንቦት 14/2018 ዓ.ም አዲስ አበባ፣
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በሀገራችን በምርምርና ልማት ዘርፍ ያለውን የመረጃ ክፍተት የሚሞላ ብሔራዊ የምርምርና ልማት ጥናት በጋራ ለማካሄድ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ።

ስምምነቱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር በለጠ ሞላ እና የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር በከር ሻሌ በጋራ ፈርመውታል።

የጥናቱ ዋና ዓላማ የምርምርና ልማት ወጪን ከሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት አንፃር ለመለካት፣ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችን ብዛት ለማወቅ፣ የምርምር ዓይነቶችን ለመለየት፣ የአሠራር ፈተናዎችንና ክፍተቶችን በማጥናት መነሻ አመልካች መረጃ ለማዘጋጀትና ከጥናቱ ከተገኙት መረጃዎች በመነሳት ተግባራዊ የሚሆኑ የፖሊሲ ምክረ-ሀሳቦችን ማቅረብ ሲሆን መረጃው ከንግድ ድርጅቶች፣ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ለትርፍ ያልተቋቋሙ የግል ድርጅቶች እንደሚሰበሰብ በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገልጿል።

ጥናቱ ለ2030 የዘላቂ ልማት ግቦች (ለኢንዱስትሪ፣ ፈጠራና መሠረተ ልማት)፣ ለአፍሪካ አጀንዳ 2063 የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ስትራቴጂ)፣ ለሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና ለኢትዮጵያ የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ስኬት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተገልጿል።
