
ነሐሴ 5/2017 ዓ.ም አዲስ አበባ፣
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎትና ኮሪያ ስታቲስቲክስ በሰው ሀይል አቅም ግንባታ ላይ በትብብር ለመስራት ከዚህ ቀደም የተፈራረሙት የጋራ ስምምነት አካል የሆነውን የአቅም ግንባታ ስልጠና ከኮሪያ ስታቲስቲክስ በመጡት ባለሙያዎች በተቋሙ ዋና መስሪያ ቤት መሰጠት ተጀመረ።

በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ ተገኝተው ስልጠናውን ያስጀመሩት የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ባከር ሻሌ ኢትዮጵያና ኮሪያ ያላቸው ግንኙነት ከልማት አጋርነት ከፍ ያለና ታሪካዊ መሆኑን ገልጸው፤ ተቋማቸው የሀገሪቱን የስታቲስቲክስ መረጃ ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችል አቅም ለማደራጀት ሪፎርም እያካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፤የሰው ሀይል ዕውቀትና ክህሎትን ማሳደግ የሪፎርም ስራው ዋና ትኩረት መሆኑን በማስረዳት ከኮሪያ ስታቲስቲክ ጋር በትብብር የሚሠጠው የአቅም ግንባታ ተግባራትም የዚሁ የሪፎርሙ ፕሮግራም አንድ አካል መሆኑን ጠቅሰው የአቅም ግንባታ ፕሮግራሙ ወደ ትግበራ እንዲገባ የቴክኒክ ድጋፍ ላደረጉ የኮሪያ ስታቲስቲክስ እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ ለሚያደርጉ የአለም አቀፍ የልማት ፕሮግራም እና ለአፍሪካ ልማት ባንክ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኮሪያ ስታቲስቲክስ ም/ዋና ዳይሬክተር Mr OH Seungcheol የኮሪያ ስታቲስቲክስ በስታቲስቲክስ ሜቴዶሎጅ፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ ቢግ ዳታና ሌሎች የዘርፋ አዳዲስ ሀሳቦች ላይ የተቋሙን ባለሙያዎች አቅም ለመገንባትና ልምድ ለማካፈል ዝግጁ መሆኑን በመግለጽ ለተደረገላቸው አቀባበል አመስግነዋል።

ለአቅም ግንባታ ፕሮግራሙ የገንዘብ ድጋፍ ያደረገው የአለም አቀፍ የልማት ፕሮግራም እና በቀጣይ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎቱን የገለጸው የአፍሪካ ልማት ባንክ የፕሮግራሙን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

የአቅም ግንባታ ስልጠናው ከተቋሙ ዋና መስሪያ ቤት ከተለያዩ ስራ ክፍል ለተውጣጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች ከኮሪያ ስታቲስቲክስ በመጡና በዘርፉ የካበተ ልምድ ባላቸው አሰልጣኞች ለሚቀጥሉት ሶስት ቀናት እንደሚሰጥ ለማወቅ ተችሏል።




