ሕዳር 4/2018 ዓ.ም፣


የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስአ አገልግሎት የስታቲስቲክስ ዲጂታላይዜሽን ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር ሜሮን ክፈለው (ዶ/ር) የተመራው ልዑካን ቡድን የደቡብ ኮሪያ የመረጃና ስታቲስቲክስ ሚኒስቴር እና ዩ.ኤን.ዲ.ፒ በትብብር ያዘጋጁት የልምድ ልውውጥና አቅም ግንባታ ስልጠና ላይ ከሕዳር 1-5/2018 ዓ.ም ከደቡብ ኮሪያ ዴጄዮን ከተማ እየተሳተፈ ይገኛል፡፡ ስልጠናው ስታቲስቲክስ ኮሪያ አሁን ላይ የደረሱበትን የመረጃ አሰባሰብ፣ አደረጃጃት፣ የመረጃ ስርጭትና ትንተና እንዲሁም የጂ.አይ.ኤስና መሰል ቴክኖሎጂ ትግበራ ላይ ያላቸውን ልምድ መሰረት በማድረግ ስልጠና እየተሰጠ ያለ ሲሆን ተቋሙ የጀመረውን ስታቲስቲክስን ማዘመን እና ወደ ላቀ ደረጃ የማድረስ እቅዱን ለማሳካት ከተጀመሩት ስራዎች መካከል የሰው ኃይል አቅም ግንባታ አንዱ የትኩረት መስክ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡

በስልጠናው መርሃ ግብር ላይ ተቋሙን በመወከል ንግርር ያደረጉት የልዑካን ቡድኑ መሪ ዶ/ር ሜሮን ክፈለው ይህ ስልጠና በሁለቱ ተቋማት መካከል በጋራ በትብብር ለመስራት ከዚህ ቀደም በ24ተኛው አለም አቀፍ የስታቲስቲክስ ኮንፈረንስ ኒዎርክ ከተማ ከተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ መሰረት በማድረግ እና በቀጣይ ተግባራዊ ሊደረግ በሂደት ላይ የሚገኘውን የስታቲስቲክስ አቅም ግንባታ ፕሮጀክትን ለማጠናከር መሰረት እንደሚጥል ገልፀው ተቋማቱ የጀመሩትን የሁለትዩሽ ግንኙነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል፡፡

ስልጠናውን እያስተባበረ የሚገኘው የመረጃና ስታቲስቲክስ ሚኒስቴር አለም አቀፍ ትብብር ዘርፍ ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ጉያንግ ሊ እንደገለፁት የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎትና ስታቲስቲክስ ኮሪያ በጋራ የጀመሩትን አቅም ግንባታና ትብብር ስራዎችን እንደሚቀጥሉ ገልፀው ከመረጃና ስታቲስቲክስና ሚኒስቴር የተላኩ ልዑካን ቡድን በአዲስ አበባ በነሐሴ ወር ለተደረገላቸው መልካም አቀባበል በተቋማቸው ስም አመስግነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ልዑካን ቡድን በደቡብ ኮሪያ እየተሰጠ ካለው ስልጠና በተጓዳኝ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንነኙት ሊያጠናክሩ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ የጋራ ውይይትና የተረመጡ ታሪካዊ ቦታዎችን እንዲጎበኙ ተደርጓል፡፡
