
ሚያዚያ 15/2018 ዓ.ም አዲስ አበባ
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት በ2018 በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት ያከናወናቸውን ተግባራት አፈፃፀም የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች፣ የዋና መ/ቤትና የ26ቱ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች በተገኙበት መድረክ ተገመገመ።


የግምገማ መድረኩን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ክቡር ዶ/ር በከር ሻሌ የኢ.ስ.አ (ከ2016-2018) በመካከለኛ ዘመን የስታቲስቲክስ ልማት እቅድ የታቀዱትን ቆጠራና ጥናቶች በስኬት ማጠናቀቁን አንስተው በ2018 በጀት ዓመት በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የተከናወነው የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ በሁለት ዙር ከመስክ መረጃ የመሰብሰብ ተግባሩ በስኬት መጠናቀቁን ገልፀው በቀጣይም የቀሩ የመረጃ ማጥራትና ሪፖርት ስራዎችን በጋራ እናጠናቅቃለን ሲሉ ገልፀዋል። ዋና ዳይሬክተሩ አክለው ለዚህ ስራ መሳካት አስተዋኦ ላደርጉ የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች፣ የስራ ኃላፊዎች፣ በስራው ለተሳተፉ መላው ሰራተኛ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።


በመድረኩ የ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት በስትራቴጂክ ጉዳዮች ስራ አስፈፃሚ አቶ ሁሴን አጎናፍር የቀረበ ሲሆን የተቋሙ የ2018 በጀት ዓመት የፊዚካል እቅድ አፈፃፀም 92.1% በመቶ መሆኑን በሪፖርቱ ተገልጿል።



በተጨማሪም በመድረኩ የግብርና ቆጠራ፣ የኢኮኖሚ ድርጀቶች ቆጠራ አፈፃፀምና በአሁኑ ሰዓት ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ተግባር እየተደረገበት በሚገኘው የመንግስት ሰራተኞች ፐርሶኔል መረጃ የማረጋገጥ ስራ ላይ ገለፃ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን በገለፃው ላይ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች በዋና ዳይሬክተር ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸው የግምገማ መድረኩ ተጠናቋል።



