ግንቦት 18/2018 ዓ.ም አዲስ አበባ፣

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ባለፉት ሶስት ተከታታይ ዓመታት ባከናወናቸው የስታቲስቲክስ ልማት ፕሮግራም የጥናትና ቆጠራዎች አፈፃፀም ቀርቦ ቀጣይ የስራ አቅጣጫ ላይ ከተቋሙ ዋና መስሪያ ቤት መላ ፈፃሚ ጋር ውይይት ተደረገ።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የስታቲስቲክስ ዲጂታላይዜሽን ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር ክብርት ዶ/ር ሜሮን ክፈለው ተቋማችን ባለፉት ሶስት ዓመታት ያከናወናቸውን ጥናቶችና ቆጠራዎች በስኬት መጠናቀቅ የሁሉም ባለሙያ የጎላ ተሳትፎ ውጤት መሆኑ እና ቀጣይ ከዚህ በተሻለ ለመስራት በስራ ክፍሎች መካከል የዕውቀት ሽግግር እንዲኖር በማድረግና የበለጠ በቅንጅት ለመስራት ለመዘጋጀት ታስቦ የተፈጠረ መድረክ መሆኑን ገልፀዋል።
በመድረኩ ከጥናቶች ስነ ዘዴ፣ ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም አንፃር፣ ከመረጃ አሰባሰብና አመዘጋገብ፣ አማራጭ የመረጃ ምንጮች ፣ የመረጃ ተደራሽነት፣ ከመረጃ አስተዳደር ማዕቀፍ አንፃር የተሰሩ ዋና ዋና ስራዎች ላይ ገለፃዎች ቀርበው ግንዛቤ ተፈጥሯል።

የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ክቡር ዶ/ር በከር ሻሌ በመድረኩ ማጠቃለያ ተቋሙ በስታቲስቲክስ ልማት ፕሮግራም የታቀዱ ስራዎችን ለመፈፀም የተቻለው የአመራሩ እና ፈጻሚው ርብርብ ፣ የባለድርሻ አካላት በቅንጅት በመስራት ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች መታገዝ ፣ አማራጭ የመረጃ ምንጮችን በመጠቀም የተሰጠውን ኃላፊነቱን የተወጣ መሆኑን ገልፀዋል።

በተጨማሪም ይህን ስኬት መነሻ በማድረግ በየደረጃ ያሉት ፈጻሚዎች በቀጣይ የበለጠ በመነሳሳት ፣የተሻሉ የቴክኖሎጂ አማራጮችን በመጠቀም ወደ ልህቀት የምናደርገውን ጉዞ ለማሳካትና የሀገራችንን የመረጃ ሉዓላዊነት ለማፅናት እና ለማላቅ ሁሉም አካላት በጋራ መስራት አለብን ሲሉ የስራ አቅጣጫ ተሰጥተዋል። ተሳታፊዎቹም ዝግጁነታቸውን የገለጹ ሲሆን የተፈጠረውን ተነሳሽነት ወደ ተሻለ ደረጃ ማሻገር እንደሚገባ ስምምነት ላይ ተደርሷል።

